ሩሲያና እና ቻይናን ጨምሮ 15 አገራት ማዕቀቡ እንዲነሳ በመጠየቅ ላይ ናቸው
ተመድ በሰሜን ኮሪያ ላይ የጣለውን ማዕቀብ እንዲነሳ ቻይና እና ሩሲያ ጠየቁ።
የመንግስታቱ ድርጅት ሰሜን ኮሪያ የአለምን ደህንነት ሊያዛቡ የሚችሉ አቶሚክ ኑክሌር እያብላላች ነው በሚል ነበር በፈረንጆቹ 2006 ዓመት ነው ማዕቀብ የጣለው።
ማዕቀቡ በዋናነት ሰሜን ኮሪያ በዓለም የምትታወቅበትን የከሰል ድንጋይ ምርት ወደ ውጭ አገራት እንዳትልክ፤ ዜጎች ወደ ፈለጉት አገራት በነጻነት እንዳይንቀሳቀሱ አድርጓል ተብሏል።
ማዕቀቡ ከሰሜን ኮሪያ መንግስት ባለፈ በዥቅተኛ ደረጃ የሚኖሩ ሰሜን ኮሪያዊያንን እየጎዳ በመሆኑ ተመድ ማዕቀቡን እንዲያነሳ ተጠይቋል።
ሩሲያ እና ቻይናን ጨምሮ 15 አገራት በሰሜን ኮሪያ ላይ ተመድ የጣለውን ማዕቀብ እንዲያነሳ የሚጠይቅ ሰነድ ማስገባታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ይህ ሰነድ ለውይይት እንዲቀርብ እና ተቀባይነት እንዲያገኝ የዘጠኝ አገራትን ድጋፍ ይፈልጋል ተብሏል።
ሁለቱ አገራት እና ሌሎች አገራትን በማስተባበር ከሁለት ዓመት በፊት ተመድ ማዕቀቡን እንዲያነሳ ጠይቀው የነበረ ቢሆንም ውጤታማ ሳይሆን ቀርቷል።
በተመድ የቻይና አምባሳደር ዛንግ ጁን እንዳሉት ድርጅቱ ማዕቀብ ከመጣል ባለፈ የሰብዐዊ ድጋፍ ለሚሹ ሰሜን ኮሪያዊያን ድጋፍ ማድረግ አለበት ብለዋል።
በፈረንጆች 2019 ዓመት ተመሳሳይ ጥያቄ ተመድ በሰሜን ኮሪያ ላይ የጣለውን ማዕቀብ እንዲያነሳ የሚጠይቅ ሰነድ ቀርቦ የነበረ ቢሆንም እልባት አልተሰጠም ያሉት አምባሳደሩ ይህ ጥያቄ ደግሞ ሊቀርብም ይችላል ብለዋል።