ሰሜን ኮሪያ አዲስ “የረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤል ሙከራ” አደረገች
አሜሪካ ይህ “የሰሜን ኮሪያ ድርጊት የዓለም ስጋት ሆና መቀጠሏን የሚያሳይ ነው” ብላለች
ፒዮንግያንግ ሙከራው “በሀገሪቱ ላይ የሚቃጣን ማንኛውንም ትንኮሳ ለመመከት” የሚያስችል መሆኑን ገልጻለች
ሰሜን ኮሪያ አዲስ የረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤል ሙከራ አደረገች፡፡
ሚሳኤሎቹ 1 ሺህ 500 ኪሎ ሜትር ርቀት የመምዘግዘግ አቅም ያላቸው እንደሆኑም ኮሪያን ሴትንራል (KCNA) የተሰኘውን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
አብዛኛውን የጃፓን መልክዓምድር የማዳረስ አቅም ያለው ነው የተባለለት የሚሳኤል ሙከራው፤ በሀገሪቱ ላይ የሚቃጣን ማንኛውንም ትንኮሳ ለመመከት እና የጠላት ኃይሎችን ወታደራዊ እንቅስቃሴ መቆጣጠር የሚያስችል መሆኑን ተመላክቷል፡፡
ሙከራው ሀገሪቱ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ያደረገቻቸው የኑክሌር ውይይቶች ባይሳኩም፤ሀገሪቱ አሁን ካለችበት የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ሆናም “አውዳሚና ወታደራዊ የጦር መሳሪያዎችን እንዴት ማሳደግ እንደምትችል ያሳየ” መሆኑንም በርካታ የፖለቲካ ልሂቃን በመናገር ላይ ናቸው፡፡
የጃፓን መንግስት ካቢኔ ጸሃፊው ካጹኖቡ ካቶ፤ የፒዮንግያንግ እርምጃ መንግስታቸው ከደቡብ ኮሪያ እና ዩናይትድ ስቴትስ ጋር በመሆን በቅርበት እየተከታተለው መሆኑ አስታውቀዋል፡፡
የደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ ክንፍ በፒዮንግያንግ የሚሳኤል ሙከራው ላይ ያለው ነገር ባይኖርም ፤ በአሜሪካ እና በደቡብ ኮሪያ የስለላ መረጃ ላይ በመመስረት በሚሳኤል ማስጀመሪያ ስፍራዎች ላይ የትንታኔ ሪፖርት በማሰናዳት ላይ መሆኑን ጠቁሟል።
“የፒዮንግያንግ ሚሳኤል ሙከራ ሪፖርቶች እየደረሱኝ ነው እናም ከአጋሮቼ ጋር እየሰራሁበት ነው” ያለው ደግሞ የአሜሪካ ጦር የኢንዶ-ፓሲፊክ ዕዝ (INDOPACOM) ነው፡፡
“የሰሜን ኮሪያ ድርጊት ሀገሪቱ ወታደራዊ መርሃ-ግብሯን በማሳደግ የጎረቤቶቿንና የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ስጋት በመሆን መቀጠሏ የሚያሳይ ነው”ም ነው ዕዙ ያለው፡፡
በሌላ በኩል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ሰሜን ኮሪያ የባልስቲክ ሚሳኤል ሙከራዎችን ከማድረግ እንድትቆጠብ በተደጋጋሚ ማስጠንቀቁ ይታወሳል፡፡
ይሁን እንጂ ፒዮንግያንግ የተመድ የጸጥታው ምክር ቤትን ማስጠንቀቂያ ችላ በማለት የምታደርገውን የባልስቲክ ሚሳኤል ሙከራ ለማስቆም በሀገሪቱ ላይ ተጨማሪ ማዕቀቦችን መጣል እንደሚስፈልግ ተንታኞች እየተናገሩ ነው፡፡
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን በአመቱ መባቻ ላይ የሀገሪቱ ሳይንቲስቶች “በዓለም ላይ በጣም ኃይለኛ ከሆኑት የጦር መሣሪያዎች ሚሳይሎችን” እየሠሩ መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል።
የአሁኑ የረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤል ሙከራ የሰሜን ኮሪያ ከፍተኛ ወታደራዊ ባለስልጣን ፓክ ጆንግ ቾን በተገኙበት የተካሄደ ነው፡፡
ፓክ ጆንግ ቾን ሁሉም የሀገሪቱን የመከላከያ ሳይንቲስቶች ወታደራዊ አቅምን ለማሳደግ እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።