ሰሜን ኮሪያ፤ በቻይና እና በሩሲያ ድጋፍ ከፀጥታው ምክር ቤት ማዕቀብ ተረፈች
ሩሲያ እና ቻይና አሜሪካ፣ ከማዕቀብ ይልቅ ንግግርን እንድታስቀድም ጠይቀዋል
አሜሪካ፤ ሰሜን ኮሪያ ላይ የተዘጋጀው ማዕቀብ ባለመጽደቁ ማዘኗን ገልጻለች
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በሰሜን ኮሪያ ላይ ሊጥለው የነበረው ማዕቀብ በሩሲያ እና በቻይና ድጋፍ ምክንያት ሳይጸድቅ ቀረ፡፡
በሰሜን ኮሪያ ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ሃሳብ የቀረበው ሀገሪቱ በዚህ ዓመት ተደጋጋሚ የሚሳኤልና ረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ጦር መሳሪያዎች ሙከራ መድረጓን ተከትሎ ነው፡፡
የማዕቀብ ሃሳቡ በአሜሪካ የቀረበ ሲሆን ማዕቀቡም ለምክር ቤቱ ቋሚና ተለዋጭ አባላት ቀርቦ ነበር፡፡ ከ15 ተለዋጭና ቋሚ አባላት መካከልም 13 ሀገራት ማዕቀቡን ሲደግፉት ቻይና እና ሩሲያ ግን ተቃውመውታል፡፡
ሞስኮ እና ቤጅንግ በምክር ቤቱ ያላቸውን ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት በመጠቀም ነው ተቃውሟቸውን ያሰሙት፡፡ በዚህም ማዕቀብ የመጣል የውሳኔ ሃሳቡ ሳይጸድቅ ቀርቷል፡፡
ሰሜን ኮሪያ “አስፈሪ የማጥቃት አቅም” መገንባቷን ትቀጥላለች- ኪም ጆንግ ኡን
የውሳኔ ሃሳቡ የትንባሆ እና የነዳጅ ምርት ወደ ሰሜን ኮሪያ እንዳይላክ የሚያስገድድ ነበር፡፡
ከዚህ በተጨማሪም አሜሪካ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ግንኙነት አለው ያለችውና ‘ላዛሩስ’ የተባለው የመረጃ በርባሪ ቡድን የማዕቀቡ አካል ነበር፡፡ ሆኖም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
በተመድ አሜሪካ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪን ፊልድ በማዕቀቡ አለመጽደቅ ማዘናቸውን በመግለጽ ``ዓለም ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮሪያ (ሰሜን ኮሪያ) በኩል ግልጽና አሁናዊ አደጋ ተደቅኖበታል`` ም ብለዋል፡፡
ዲፕሎማቷ፤ ሰሜን ኮሪያ በዚህ ዓመት ስድስት ጊዜ አህጉር አቋራጭ ባልስቲክ ሚሳኤል ማስወንጨፏንና የኒዩክለር ሙከራ ለማድረግ እየተዘጋጀች መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከአሜሪካ ተወካይ በተጨማሪም የብሪታኒያ፣ የፈረንሳይና የደቡብ ኮሪያ ተወካዮችም ተመሳሳይ አስተያየት መስጠታቸው ተገልጿል፡፡
በተመድ የቻይና እና የሩሲያ ተወካዮች ፤ አሜሪካ አስቀድሞ ማዕቀብን ከማሰብ ንግግርን ማጎልበት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡