ሰሜን ኮሪያ “አስፈሪ የማጥቃት አቅም” መገንባቷን ትቀጥላለች- ኪም ጆንግ ኡን
የአህጉር አቋራጭ ሚሳዔል ሙከራው የአሜሪካ ወታደራዊ እርምጃ ለመከላከል የሚረዳ ነው
ሰሜን ኮሪያ ግዙፉን ህዋሰኦንግ-17 አህጉር አቋራጭ ሚሳዔል ሙከራ አድርጋለች
ሰሜን ኮሪያ “ለማንም የማይታለል እና የማይገዛ አስፈሪ የማጥቃት አቅም መገንባቷን እንደምትቀጥል” የሀገሪቱ መሪ ኪም ጆንግ ኡን አስታወቁ።
ኪም ጆንግ ኡን ባሳለፍነው ሀሙስ በተካሄደው እና በሀገሪቱ ግዙፍ በተባለለት የሚሳዔል ሙከራ ላይ የተሳተፉ ሰራተኞችን በጎበኙበት ወቅት ይህንን መናገራቸውን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ሰሜን ኮሪያ ባለፍነው ሀሙስ “አውሬው” የሚል መጠሪያ የተሰጠውን ግዙፉን ህዋሰኦንግ-17 አህጉር አቋራጭ ሚሳዔል (አይ.ሲ.ቢ.ኤም) ሙከራ ማድረጓ ይታወሳል።
ኪም ጆንግ ኡን በሚሳዔል ማስንጨፍ ሙከራ ላይ ከተሳተፉ ሳይንቲስቶች፣ ቴክኒሻኖች እና ሌሎችም ሰራተኞችን አግኝተው ማናገራቸው ተሰምቷል።
“የሚፈራ የማጥቃት አቅም በሚኖረን ጊዜ ያለንን ወታደራዊ አቅም ማንኛውም አካል ሊያቆመው አይችልም” ያሉት ኪም፤ “ማንም ሰው ጦርነትን ማስቀረት አይችልም፤ ነገር ግን በኢምፔሪያሊስቶች የሚደረጉ ትንኮሳዎችን መቆጣጠር የሚቻለው በጠንካራ ሰራዊት ነው” ብለዋል።
ሀገራቸው ሰሜን ኮሪያ ባሳለፍነው ሀሙስ ያካሄደችው ህዋሰኦንግ-17 አህጉር አቋራጭ ሚሳዔል (አይ.ሲ.ቢ.ኤም) ሙከራ አሜሪካ የምትወስደውን ማንኛውንም ወታደራዊ እርምጃ ለመከላከል የሚረዳ መሆኑን ኪም ተናግረዋል።
ኪም ጆን ኡን አክለውም የመከላከያ ኃይላቸው ለማንም የማይገዛ እና የማይታለል፤ ከባድ ፈተናዎች እና ችግሮች ቢያጋጥሙትም በፅናት እንደሚቆይ ተናግረዋል።
ኪም የሀገሪቱን የኒውክሌር ሃይል እንደማሳያነት በመጥቀስ ሰሜን ኮሪያ "ፍፁም የሆነ እና ጠንካራ ስትራቴጂካዊ ሀይል መገንባቷን ትቀጥላለች" ብለዋል።