ኢትዮጵያ፤ ፈረንሳይ እና ቻይና ላቋቋሙት የብድር ኮሚቴ አዲስ የእዳ ሽግሽግ ጥያቄን አቀረበች
ኢትዮጵያ 30 ቢሊዮን ዶላር ገደማ የውጭ ብድር እንዳለባት ይነገራል
ጥያቄው ጊዜ ያለፈባቸውን ስምምነቶች በአዲስ በመተካት ለድህነት ቅነሳ የሚሆኑ ሀብቶችን በቅናሽ ለማግኘት የሚያስችል ነው ተብሏል
ኢትዮጵያ አዲስ የተራዘመ ብድር ስምምነት ጥያቄን በቅርቡ ለተቋቋመው ዓለም አቀፍ የአበዳሪዎች ኮሚቴ አቀረበች፡፡
የብድር ኮሚቴው ቀደም ሲል ኢትዮጵያ ባቀረበችው ጥያቄ መሰረት በፈረንሳይ እና ቻይና ጥምረት የተቋቋመ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ባሳለፍነው የካቲት ለደሃ ሃገራት የብድር ማሻሻያዎችን በማድረግ እፎይታ ሊያስገኝ የሚችልና በቡድን 20 አባል ሃገራት ባስቀመጡት ማዕቀፍ መሰረት የሚሰራ የብድር ኮሚቴ እንዲቋቋም አይ ኤም ኤፍን ጠይቃ ነበር፡፡
ጥያቄውን ተከትሎ ፈረንሳይ እና ቻይና የብድር ኮሚቴውን አቋቁመው የኮሚቴውን የመጀመሪያ ስብሰባ ከሰሞኑ አካሂደዋል፡፡
በስብሰባው የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ተሳትፈዋል፡፡
ስብሰባውን በማስመልከት መግለጫ ያወጣው ሚኒስቴሩ የብድር ኮሚቴው በቡድን 20 አባል ሃገራት በተቀመጠው ማዕቀፍ መሰረት የዕዳ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት የወሰዳቸውንና “ወሳኝ” ያላቸውን እርምጃዎች መቀበሉን አስታውቋል፡፡
ኮሚቴው የብድር ጫናዎችን በማቅለል ምጣኔ ሃብቷን ለማረጋጋት በምታደርገው ጥረት ኢትዮጵያን ለመደገፍ ላሳየው ቁርጠኝነት ያለውን አድናቆትም ገልጿል፡፡
ለዚህም ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ ማመስገናቸው በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡
የኮሚቴው ይህን ማድረግ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ያጋጠሙ ምጣኔ ሃብታዊ ችግሮችን በመቋቋም የብድር እፎይታዎችን ሊያስገኝ እና የመልማት ፍላጎቶችን ለማሳካት የሚያስችልን ገንዘብ ለማግኘት ያግዛል እንደ ሚኒስቴሩ መግለጫ፡፡
የብድር ሁኔታዎቹን ለማጠናቀቅ በሚያስችሉ ስራዎች ዙሪያ ከአበዳሪዎቹ ጋር ለመስራት ያለውን ቁርጠኝነትም ገልጿል፡፡
ሚኒስቴሩ በመግለጫው መንግስት ሃገር በቀል ምጣኔ ሃብታዊ ዕቅዶችን ሳያወላውል በመተግብሩ የተረጋጋ እድገት ያለው ጠንካራ ምጣኔ ሃብት ለማስስመዝገብ መቻሉን አስቀምጧል፡፡
ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) በተራዘመ ብድር እና በተራዘመ ፈንድ የኢትዮጵያን ምጣኔ ሃብት ለመደገፍ ላደረገው ጠቃሚ አስታዋጽኦም እውቅና ሰጥቷል ቀጣይ የሚኖረው ተሳትፎ ወሳኝ እንደሆነ በመጠቆም፡፡
የተራዘመ የብድር ስርዓት የቴክኒክ ማብቂያ ቢኖረውም የፈንድ ስርዓቱ አለማብቃቱን ያስታወቀው ሚኒስቴሩ ጊዜው ያለፈበትን ክፍል በመተካት ለድህነት ቅነሳ የሚሆኑ ሀብቶችን በቅናሽ ለማግኘት የሚያስችለንን አዲስ የተራዘመ ብድር ዝግጅት ጠይቀናል ብሏል።
ከአይ ኤም ኤፍ ጋር በሚኖሩ ቀጣይ ግንኙነቶች ዙሪያ ለመወያየት ዝግጁ መሆኑንም ለሃገር በቀል ምጣኔ ሃብታዊ እቅድ ትግባራዊነት ድጋፍ ያደረጉ ዓለም አቀፍ አጋሮችን ያመሰገነው ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡
ኢትዮጵያ 30 ቢሊዮን ዶላር ገደማ የውጭ ብድር እንዳለባት ይነገራል፡፡