የመጠባበቂያ ጋዙ ለቤጂንግና አካባቢው በትንሹ የአንድ ዓመት ፍጆታቸውን ይሸፍናል ተብሏል
ቻይና 10 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የተፈጥሮ ጋዝ ማከማቸቷን ገለጸች።
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦርን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከሩሲያ ጋር ወደ ጦርነት በመግባቷ የዓለም ነዳጅ እና ምግብ ዋጋ አሻቅቧል።
ከሳውዲ አረቢያ በመቀጠል ሁለተኛዋ የዓለማችን ነዳጅ ላኪ የሆነችው ሩሲያ ላይ የተለያዩ ማዕቀቦች መጣላቸውን ተከትሎ በርካታ ሀገራት የነዳጅ እና የተፈጠሮ ጋዝ ፍላጎታቸውን አሳድገዋል።
የሀገራት የነዳጅ እና የተፈጠሮ ጋዝ ፍላጎት ለማደጉ ዋነኛው ምክንያት የሩሲያ ነዳጅ ወደ ገበያ ላይቀርብ ይችላል እንዲሁም የነዳጅ እጥረት ሊያጋጥም ይችላል በሚሉ ምክንያቶች ሀገራት የመጠባበቂያ ነዳጅ ፍለጋ ላይ ናቸው።
ቻይናም 10 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የተፈጥሮ ጋዝ በሰሜናዊ የሀገሪቱ ግዛቶች አካል በሆነችው ቲያንጂን ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ማከማቸቷንአስታውቃለች።
እንደ ሽንዋ ዘገባ ከሆነ ይህ ከፍተኛ መጠን ያለው ጋዝ የሀገሪቱ ዋና ከተማ የሆነችው ቤጂንግን ጨምሮ በአካባቢው ላሉ ከተሞች የአንድ ዓመት ፍጆታን ይሸፍናል ተብሏል።
ነዳጁን ከ22 ዓመት በፊት የተገነባው ዳዛንግቱ የተሰኘው የቻይና ነዳጅ አከፋፋይ የንግድ ድርጅት ለሸማቾች በመሬት ውስጥ በዘረጋው የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር በኩል ይቸረችራልም ተብሏል፡፡
ቻይና 10 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር መጠን ጋዝ መከዘን የሚያስችሉ 10 መጋዝኖች ያሏት ሲሆን፤ የቻይና ብሄራዊ የፔትሮሊየም ኮርፖሬሽን ሁሉንም መጋዝኖች በበላይነት ያስተዳድራቸዋል፡፡
የቻይና ዓመታዊ የተፈጥ ጋዝ ፍላጎቷ በየጊዜው እያደገ ሲሆን በ2025 ዓመት የሀገር ውስጥ የነዳጅ ፍላጎት ወደ 230 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ከፍ እንደሚል ይጠበቃል፡፡
ቻይና የሩሲያን ነዳጅ ከመግዛት እንድትቆጠብ በአሜሪካ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያዎች ቢደርሷትም ቻይና ግን የሩሲያን ጨምሮ ከኢራን እና ሌሎች ሀገራት ነዳጅ በገፍ በመግዛት ላይ ትገኛለች።