ቻይና የጡረታ መውጫ ጊዜን ለማራዘማ ማቀዷ ተቃውሞ ቀሰቀሰ
በየአመቱ ጡረታ የሚወጡ ዜጎቿ ቁጥር የጨመረባት ሀገር ለጡረታ ክፍያ የምታወጣው ወጪ ተጽእኖ እየፈጠረባት ነው ተብሏል
በውለደት ምጣኔ መቀነስ የሰራተኛ ሀያሏ ማሽቆልቆል ሀገሪቱ የጡረታ ጊዜ የማራዘም ውሳኔ ላይ እንድትደርስ ተጨማሪ ምክንያት ነው
ቻይና የዜጎቿን ጡረታ መውጫ ጊዜ ለማራዘም ማቀዷ ተቃውሞ ማስነሳቱ ተሰምቷል፡፡
የውለደት ምጣኔዋ ሲቀንስ በአንጻሩ በእርጅና እድሜ ላይ የሚገኙ በርካታ ዜጎች ባለቤት የሆነችው ቤጂንግ የስነ ህዝብ ፖሊሲዋን ከኢኮኖሚ ግስጋሴዋ ጋር ለማስቀጠል የጡረታ አድሜን ማራዘም የተሻለ አመራጭ እንደሚሆን ወጥናለች፡፡
በአለም አቀፍ ደረጃ የውልደት መጠናቸው በከፍተኛ ደረጃ ከቀነሰባቸው ሀገራት መካከል በሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝው ሀገር ከ1950 – 2021 ባለው አመት የውልደት ምጣኔዋ በ81 በመቶ እንደቀነሰ ይነገራል፡፡
በ2022 የወጡ መረጃዎች 280.4 ሚሊየን ወይም 19 በመቶ ቻይናውያን 60 አመት እና ከዛ በላይ በሚሆን እድሜ ላይ እንደሚገኙ ይጠቁማሉ፡፡
ይህን ተከትሎም በየአመቱ በእድሜ ምክንያት ከስራው አለም የሚገለሉ ዜጎች ቁጥር መጨመር በኢኮኖሚው ላይ ከሚያሳድረው ተጽእኖ ባለፈ ሀገሪቱ ለጡረተኞች የምትከፍለው የጡረታ ክፍያ ወጪ እንዲጨምር አድርጓል ነው የተባለው፡፡
ፖሊሲ አውጭዎች በእርጅና ላይ የሚገኙ ዜጎች እያደገ መምጣት በ2035 የቻይና የጡረታ ፈንድ ተቀማጭ እንዲያልቅ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል አስጠንቅቀዋል፡፡
ባሳለፍነው አመት በጡረተኞች የህክምና ሽፋን ወጪ ላይ ቅነሳ መደረጉን ተከትሎ መንግስት የገጠመውን የጡረታ ፈንድ እጥረት ለመቅረፍ የዜጎችን ተቀማጭ እየተጠቀመ ነው በሚል በቻይና ዋና ዋና ከተሞች ላይ ጡረተኞች የተቃውሞ ሰልፍ አድርገው እንደነበር ይታወሳል፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ በከተማ የሚገኙ ወንዶች በ60 አመታችው ጡረታ ሲወጡ ሴቶች ከ50-55 ባለው ጊዜ ስራ ያቆማሉ፡፡
የሀገሪቱ አስተዳደር በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ይፋ ባደረገው የጡረታ መውጫ አድሜ የማራዘም እቅድ የእድሜ ገደቡን በግልጽ ባያሳውቅም የተለያዩ የስነ ህዝብ ፖሊስ አጥኚዎች እስከ 65 አመት ድረስ ሊራዘም እንደሚችል ትንበያቸውን አስቀምጠዋል፡፡
ካሳለፍነው እሁድ ጀምሮ በቻይና ዋና ዋና የማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ አዲሱ የጡረታ እቅድ በርካታ ዜጎች መነጋገርያ ሆኖ የቆየ ሆኖ ሰንብቷል፡፡
“ሻውሀንግሹ” በተባለው እንደ ኢንስታግራም አይነት የቻይና ማህበራዊ ትስስር ገጽ ላይ 100 ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎች ከጡረታ መውጫ አድሜ ጋር በተያያዘ ይፋ ስለተደረገው እቅድ ሀሳባቸውን መሰንዘራቸውን ሲኤንኤን አስነብቧል፡፡
1.4 ቢሊየን ህዝብ ባላት ሀገር ውስጥ በእድሜ የገፉ ሰዎች የሰራ ቆይታ የሚራዘም ከሆነ የወጣቶችን የስራ አድል ይሻማል የሚሉ ወጣቶች እና የጡረታ ጊዜያቸው የተራዘመባቸው በእድሜ የገፉ ሰዎች ተቃዎሟቸውን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡