ስራ ለመቅጠር የእርግዝና ምርመራ የሚጠይቁት የቻይና ኩባንያዎች
ድርጊቱ በተደጋጋሚ ይፈጸምበታል በተባለው ምስራቅ ቻይና በሚገኙ 16 ድርጅቶች ላይ ክስ ተከፍቷል
ረጂም የወሊድ ፈቃድ አሰላችቶናል ያሉት ኩባንያዎች አዳዲስ እና ነባር ሰራተኞቻቸው የእርግዝና ምርመራ እንዲያደርጉ እያስገደዱ ነው
ስራ ለመቅጠር የእርግዝና ምርመራ በሚጠይቁት የቻይና ኩባንያዎች ላይ ቅጣት ለመጣል ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝ ተሰምቷል።
ሴቶች ለወሊድ የሚወስዱት ረጂም የእረፍት ጊዜ እና የወሊድ ጥቅማ ጥቅም ክፍያ የድርጅታችን ምርታማነት ላይ ተጽእኖ ፈጥሯል ያሉት የቻይና ኩባንያዎች አዳዲስ ሴት ሰራተኞችን ከመቅጠራቸው በፊት የእርግዝና ምርመራ እንዲያቀርቡ በአስገዳጅነት እንደሚጠይቁ ነው የተነገረው።
ተቋማቱ ከአዳዲስ ሰራተኞች ባለፈ ነባር ሰራተኞች በየጊዜው በተመሳሳይ ምርመራ እንዲያደርጉ በማስገደድ የሀገሪቱን የሴቶች መብት በመጣስ ክስ ተከፍቶባቸዋል።
በምስራቅ ቻይና ጂንግሱ በተባለ ግዛት በሚገኙ መሰርያ ቤቶች ላይ ድርጊቱ በተደጋጋሚ እንደሚፈጸም ጥቆማ የደረሰው የአካባቢው የፍትህ ቢሮ ባደረገው ምርመራ እስካሁን ከ168 በላይ ሴቶች በ16 ተቋማት የእርግዝና ምርመራ እንዲያደርጉ መጠየቃቸውን ደርሶበታል።
ድርጊቱ ህግ ወጥ እንደሆነ የሚያውቁት ተቋማቱ በተቋማቸው የሰው ሀይል ፖሊሲ እና ህገ ደንብ ላይ አሰራሩን ያላከተቱ ሲሆን፤ ሴቶች ምርመራውን እንዲያደርጉ የሚጠይቁት በስራ ቃለ መጠይቅ ወቅት በመሆኑ የፍትህ ቢሮው ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስዶ ክስ ለመመስረት የማስረጃ እጥረት እንዲያጋጥመው ምክንያት ሆኗል።
ሆኖም የምርመራ ዶሴው ተቋማቱ እርጉዝ ሆነው የተገኙ ሴቶችን ስራ ላለመቅጠር የወሰኑትን ውሳኔ በማስረጃነት ሊቀርብባቸው እንደሚችል ነው የተነገረው።
ተቋማቱ የእርግዝና ምርመራውን ውጤት የሚጠይቁት ለእርጉዝ ሴቶች በሚሰጠው ከፍተኛ የጥቅማጥቅም እና ረጂም የወሊድ እረፍት በመሰላቸታቸው ነው ተብሏል።
የሴቶችን እኩል ስራ የማግኝት መብት ጥሷል በተባለው አሰራር መስርያ ቤቶቹ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ 50ሺ ዩዋን ወይም 6900 ዶላር ቅጣት ይጠብቃቸዋል።
ሴቶች እኩል የስራ እድል እና ክፍያ አያገኙባቸውም ከሚባሉ የእስያ ሀገራት መካከል አንዷ በሆነችው ቻይና ህግ መሰረት በስራ ቅጥር ወቅት ሴቶች ስለትዳር ሁኔታቸው እና ልጅ ስለመውለድ ስላላቸው እቅድ እንዳይጠየቁ ይደነግጋል።
ሆኖም በሀገሪቱ የመንግስት ተቋማትን ጨምሮ ከሴቶች ይልቅ ወንዶች ስራ የመቀጠር እድላቸው ከፍተኛ ነው።
በሀገሪቱ ብሄራዊ ሲቪል ሰርቪስ ከሚገኙ 40ሺህ የስራ አይነቶች መካከል አስር ሺህ 981 ስራዎች ወንዶች ብቻ እንዲሰሯቸው የተፈቀዱ የሰራ አይነቶች ሆነው ተዘርዝረዋል።