ቻይናዊያን ራሳቸው ከማግባት ይልቅ ውሾቻቸውን በማጋባት ተጠምደዋል ተባለ
በቻይና ውሻን ጨምሮ ለቤት እንስሳት በዓመት ከ38 ቢሊዮን በላይ ዶላር ወጪ ይደረጋል
የህዝብ ቁጥሯ እየቀነሰባት ያለችው ቻይና ትዳር ለሚመሰርቱ እና ልጅ ለሚወልዱ ዜጎቿ የተለያዩ ማበረታቻዎችን ዘርግታለች
በቻይና የውሻ ጋብቻ ደርቷል ተባለ፡፡
የዓለማችን ሁለተኛዋ ባለ ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት በሆነችው ቻይና ለውሾች ጋብቻ በሚል የሚዘጋጁ ድግሶች ቁጥር እየጨመረ ነው ተብሏል፡፡
በሀገሪቱ ዋና ዋና ከተሞች ከሰዎች ጋር የሚኖሩ ድመት እና ውሾች ከ116 ሚሊዮን በላይ ነው የተባለ ሲሆን ውሾችን እና ድመቶች ድል ባለ ሰርግ መዳር እየጨመረ መጥቷል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በየ አዳራሾች ውሾችን ቬሎ በማልበስ ኬክ እና ሌሎች የሰርግ ማድመቂያ ዝግጅቶችን ማዘጋጀት እየጨመረ ይገኛል ተብሏል፡፡
ሊንግ እና ጊጂ የተሰኙ ጥንዶች ለሮይተርስ እንዳሉት ከፍቅረኛው ጋር በቅርቡ የመጋባት እቅድ እንደሌላቸው ተናግረው ከእነሱ በፊት ግን አብራቸው የምትኖር ውሻቸውን መዳር እንደሚፈልጉም ጠቅሰዋል፡፡
የሂሳብ መምህራንን ለመቅጠር አስገራሚ ማስታወቂያ ያወጣው የህንድ ትምህርት ቤት
በ2022 ኬክ ቤት የከፈተው አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ ቻይናዊ በበኩሉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለውሾች ሰርግ ማድመቂያ የሚሆኑ ኬኮችን እንዲያቀርብላቸው የሚጠይቁት ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው ብሏል፡፡
በቻይና በአጠቃላይ ለውሻ እና ድመት በሚል የሚወጣው ዓመታዊ በጀት እየጨመረ ነው የተባለ ሲሆን በ2023 ብቻ ከ38 ቢሊዮን ዶላር በላይ ደርሷል፡፡
ቻይና በየዓመቱ የሚወለዱ ህጻናት ቁጥር እያሽቆለቆለ ሲሆን የሀገሪቱ መንግስትም ይህንን ለመቀልበስ በሚል ለሚጋቡ ጥንዶች እና ልጅ ለሚወልዱ ዜጎች የተለያዩ ማበረታቻዎችን አዘጋጅቷል፡፡
ለበርካታ አስርት ዓመታት ዓለማችን ቁጥር አንድ የህዝብ ብዛት የነበራት ቻይና ባሳለፍነው ዓመት በሕንድ መበለጧ ይታወሳል፡፡