ሴቶች ሀብታም ወንድ እንዲያገቡ የምታሰለጥነው ቻይናዊት በአመት 19 ሚሊየን ዶላር እያገኘች ነው
የቀድሞዋ ዘፋኝ “ገንዘብን አሳዱ” እያለች ከምትመክራቸው ሰዎች ጠቀም ያለ ገንዘብ እያገኘች ነው ተብሏል
አስተምሮዋ የማህበረሰቡን ወግና ባህል ይቃረናል የሚል ተቃውሞ ቢበዛባትም የህይወት መስመራችን አስተካክላለች የሚሉ ደጋፊዎችም አሏት
በቻይና ሴቶች እንዴት ሀብታም ወንዶችን ማግባት እንደሚችሉ የምታሰለጥነው ወጣት ሀብት እያካበተች ነው ተባለ።
“ኩ ኩ” በሚለው የማህበራዊ ገጽ ስሟ የምትታወቀው ለ ቹዋንጉ ባለፈው አመት ነው የማህበራዊ ሚዲያውን የተቆጣጠረችው።
አወዛጋቢዋ የኢንተርኔት ተጽዕኖ ፈጣሪ በአጭር ጊዜ በርካታ ተከታዮችን ያፈራች ሲሆን፥ የምታነሳቸው ሃሳቦች ግን እንደ ዌይቦ ካሉ የማህበራዊ ትስስር ገጾች እንድትታገድ አድርጓታል።
“ኩ ኩ” የፍቅር ግንኙነትም ሆነ ትዳር ገንዘብ የሚገኝበት “ማህበረሰባዊ መሰላል ነው” ብላ ታምናለች።
የአሜሪካውን ግዙፍ አማካሪ ተቋም ስያሜ ተውሳም “የፍቅር ግንኙነት ማኬንሲ” ነኝ ብላ ራሷን የምትጠራው ለ ቹዋንጉ፥ በምትለቃቸው ቪዲዮዎች ሁሉም የፍቅር ግንኙነቶች ጥቅም(ገንዘብ) ሊያስገኙ ይገባል እያለች ስትሞግት ትደመጣለች።
“የትኛውም የፍቅር ግንኙነት ጥቅሜን የሚያሳድግና ቀጣይ ህይወቴን የሚያቀና መሆን አለበት” ስትልም ትገልጻለች።
የቀድሞዋ ዘፋኝ የአሁኑ የፍቅር አጋሯን እንዴት እንደመረጠችው ስትገልጽም 4 ሚሊየን ዩዋን (550 ሺህ በላይ ዶላር) ጥሎሽ እንደሚሰጣት እንደነገራት ታወሳለች።
አድናቂዋ እና የትዳር አጋሩ እንድትሆን የጠየቃት በ15 አመት የሚበልጣት ሰውም በየወሩ 4 ሺህ ዶላር ሊሰጣትና 2 ነጥብ 8 ሚሊየን ዶላር የሚያወጣ ቤት በሻንጋይ ሊገዛላት ቃል ገብቶ እንደነበር ነው የገለጸችው።
ይሁን እንጂ ከገንዘቡ ይልቅ የወደፊት ህልሙ ያሳመነኝ የአሁኑ ፍቅረኛየ በመሆኑ ከእርሱ ጋር መቀጠልን መርጫለሁ ብላለች።
በአንድ በኩል ገንዘብን አሳዱ እያለች እየመከረች ለራሷ ሲሆን ግን ፍቅርን አስቀድማለች የሚሉ ትችቶች ቢሰነዘሩባትም “ፍቅረኛየ ነገ የምፈልገውን እንደሚያሳካልኝ ስላመንኩ ነው” የሚል አጭር ምላሽ ትሰጣለች።
“ኩ ኩ” በኦንላይን ለሚከተሏት ሰዎች ነቀፌታ የበዛበትን አስተምሮዋን ለማስተላለፍ “ገንዘብ” እና “እርግዝና” ለሚሉ ቃላት የራሷን አዳዲስ ቃላት የፈጠረች ሲሆን፥ የማህበራዊ ትስስር ገጿን ከመዘጋት ለመታደግ ሰው ሰራሽ አስተውሎትንም ትጠቀማለች።
የፍቅር ግንኙነትም ሆነ ትዳር ጥቅም የሚጋራበት ነው ብላ የምታምነው በግል እና በተለያዩ መድረኮች እየተገኘች የማማከር ስራ እየሰራች ነው ብሏል ሳውዝ ቻይና ሞርኒንግ ፖስት በዘገባው።
በአመት 142 ሚሊየን ዩዋን (19 ሚሊየን ዶላር በላይ) እያገኘች ነው የሚለው ዘገባው በቀጥታ ስርጭቷ ምክር ለማግኘት 155 ዶላር እንደምታስከፍል ያነሳል።
“ውጤታማ ግንኙነት” ለሚለው ታዋቂ ስልጠናዋ ደግሞ 480 ዶላር ታስከፍላለች።
በግል ወጣቷን አግኝቶ ለማነጋገር በየወሩ ቢያንስ 1400 ዶላር መክፈል ይጠበቅበታል የሚለው ዘገባው፥ የቹዋንጉ ጉዳይ ቻይናውያንን ለሁለት መክፈሉን ይጠቅሳል።
አስተምሮዋ የማህበረሰቡን ወግና ባህል ይቃረናል የሚል ተቃውሞ የሚያነሱባት እንዳሉ ሁሉ የህይወት መስመራችን አስተካክላለች የሚሉ ደጋፊዎቿ ቁጥርም ቀላል የሚባል አይደለም።
ከምታማክራቸው ሰዎች የምታገኘው ገንዘብም የተከታዮቿን መበራከት ያሳያል ነው የሚለው።