የቻይና የጦር ልምምድ ትናንት ይጠናቀቃል ቢባልም ልምምዱ እንደቀጠለ ነው
ቻይና የአሜሪካ አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ ታዋንን መጎብኝቷን ተከትሎ ነበር የጦር ልምምዱን የጀመረችው
የቻይና የጦር ልምምድ ትናንት ይጠናቀቃል ቢባልም ልምምዱ እንደቀጠለ ነው
ቻይና በታይዋን አቅራቢያ የጀመረችው የጦር ልምምድ እንደቀጠለ ነው።
የአሜሪካ ምክር ቤት አፈጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ ታይዋንን ጨምሮ አምስት የእስያ ሀገራትን መጎብኘታቸውን ተከትሎ በሩቅ ምስራቅ የነገሰው ውጥረት እንደቀጠለ ነው።
አፈ ጉባኤዋ ባሳለፍነው ሳምንት ታይዋንን የጎበኙ ሲሆን ድርጊቱ ቻይናን እንዳስቆጣ የዓለም ብዙሀን መገናኛዎች ዘግበዋል።
ይሄንን ተከትሎም ቻይና በታይዋን ባህር ዙሪያ እስከ ቀጣዩ ትናንት ድረስ የሚቆይ ወታደራዊ ልምምድ በማድረግ ላይ መሆኗን አሳውቃ ነበር።
ይሁንና የቻይና ወታደራዊ የጦርነት ልምምድ ትናንት ያበቃል ተብሎ ቢጠበቅም ልምምድ ዛሬም እንደቀጠለ ሲጂቲኤን አፍሪካ ዘግቧል።
የቀጠለው ወታደራዊ ልምምድም የአየር፣የባህር እና የየብስ ጦርነት ልምምድ ሲሆን ታይዋን እና የቡድን ሰባት ሀገራት ልምምዱን ተችተዋል።እንደ ዘገባው ከሆነ ቻይና በታይዋን 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በስድስት አቅጣጫ የጦርነት ልምምዱ እንደቀጠለ ይገኛል ተብሏል።
ቻይና ባሳለፍነው ሳምንት ልምምድ ላይ ዶንግ ፋንግ የተሰኘው የቻይና የረጅም እና አጭር ርቀት ባልስቲክ ሚሳኤሎች ወደ ታይዋን ባህር ተኩሳለች።
በታይዋን ስድስት አቅጣጫዎች ምንም አይነት የባህር እና አየር ላይ ትራንስፖርት እንቅስቃሴ እንዳይኖር ቻይና አስቀድማ ማስጠንቀቋ ይታወሳል ።ታይዋን የቻይና ድርጊት የጦርነት ትንኮሳ መሆኑን አስታውቃ እስከ እሁድ የሚቆየውን የጦር ልምምድ እንደማትታገሰው አስቀድማ ተናግራም ነበር።
በቀጠለው የቻይና በታይዋን ባህር አቅራቢያ የጀመረችው የጦር ልምምድ ታይዋን እስካሁን በይፋ የሰጠችው መግለጫ የሌለ ሲሆን ቻይናም ልምምዱ እስከመቼ እንደሚቀጥል አላሳወቀችም።