ሁለት እጆች ስለሌላት እግሮቿን እንደ እጆቿ በመጠቀም ሀገር አቀፍ ፈተና እየወሰደች ያለች ተማሪ
ተማሪ ኬይራ ጀማል “አካል ጉዳተኝነት ከምፈልገው መዳረሻ የሚያግደኝ ሳይሆን ይበልጥ የሚያተጋኝ ነው” ብላለች
ተማሪ ኬይራ ፈተናውን በተሻለ ውጤት በማለፍ በሚቀጥለው ዓመት ወደ ዩኒቨርሲቲ እንደምትገባም ተስፋ ሰንቃለች
ሁለት እጆች ስለሌላት ስለሌላት እግሮቿን እንደ እጆቿ በመጠቀም ሀገር አቀፍ ፈተና እየወሰደች ያለችው ተማሪ ኬይራ ጀማል ቀልብ ስባለች።
በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ የተፈጥሮ ሳይንስ ፈተና እየሰጡ ይገኛሉ።
ተማሪ ኬይራ ጀማልም በተፈጥሮ ሁለት እጆች የሌላት የ12ኛ ክፍል የተፈጥሮ ሳይንስ ተፈታኝ ስትሆን በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፈተናውን እየወሰደች መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።
መምህራንና የዩኒቨርሲቲው አመራር በተማሪዋ ብቃት እና ችሎታ ብቻ ሳይሆን ባላት የስነ ልቦና ጥንካሬ እና መተማመን ይደመሙባታል።
የ2ኛ ደረጃ ትምህርቷን በማሪያም ሰፈር 1ኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምሀርት ቤት ያጠናቀቀች ሲሆን በቆይታዋ ታታሪና የደረጃ ተማሪ መሆኗን መምህራኖቿ ይመሰክራሉ።
ፈተናውን በአንድ ድጋፍ ሰጪ መምህር በመታገዝ እግሮቿን እንደ እጆቿ በመጠቀም በበይነ መረብ እየተፈተነች ስትሆን የኮምፒውተሩን ማውዝ የምትጠቀመው በእግሮቿ ነው።
ተማሪ ኬይራ ጀማል ለኢዜአ እንደተናገረችው፤ አካል ጉዳተኝነት ከምትፈልግበት ስፍራና ጎዳና የማያግዳት ይበልጥ የሚያተጋት አጋጣሚ ነው።
ፈተናውን በበቂና በተሻለ ውጤት በማለፍ በሚቀጥለው ዓመት ወደ ዩኒቨርሲቲ እንደምትገባም በሙሉ ልብ ተናግራለች።
ዛሬ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የተጀመረውን የተፈጥሮ ሳይንስ ሀገር አቀፍ ፈተና ያስጀመሩት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ሀርቢ ቡህ “ተማሪ ኬይራ ለሌሎች አካል ጉዳተኞች ምሳሌ ናት፤ ያላትን ጥንካሬ አድንቄያለሁ፤ የምትፈልገው ደረጃ እንደምትደርስ ተስፋ አለኝ “ብለዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሱልጣን አልይ በበኩላቸው፤ ተማሪ ኬይራ ጀማል አካል ጉዳተኝነት አለመቻል አለመሆኑን በተግባር እያሳየች መሆኗን ገልፀዋል።