ፀረ ራዳርን ጨምሮ ከአየር ወደ ምድርና ወደ ውሃ የሚወነጨፉ ሚሳዔሎችን የመታጠቅ አቅም አለው
ቻይና ካሏት ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች ውስጥ “CH-7 ስቲልዝ” በመባል የሚጠራው ድሮን አንዱ እንደሆነ ይነገራል።
CH-7 ድሮን “ቀስተ ደመና” የሚል መጠሪያ ያለው ሲሆን፤ በፈረንጆቹ 2018 ላይ ነበረ ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ የተደረገው።
ድሮኑ ክንፍ 22 ሜትር ሚረዝም ሲሆን፤ አጠቃላይ ቁመቱ ደግሞ 10 ሜትር ነው፤ የድሮኑ አጠቃላይ ክብደትም 6500 ኪሎ ግራም እንደሆነም ነው የሚነገረው።
በአየር ላይ በአንድ ጊዜ ያለማቋረጥ ለ15 ሰዓታት ማገልገል የሚችለው ድሮኑ፤ 3500 ኪሎ ሜትሮችን ማካለል እንደሚችልም ታውቋል።
የቻይና CH-7 ድሮን ከምድር ከ10 እስከ 13 ኪሎ ሜትር ከፍታ ላይ በሰዓት ከ900 ኪሎ ሜትር በላይ መብረር የሚችል መሆኑም ተነግሯል።
ቻይና CH-7 ድሮንን ምን የተለየ ያደርገዋል
ድሮኑ የፀረ ጨረር (አንቲ-ራዲየሽን) ሚሳዔሎችን ጨምሮ ሌሎችን ወታደራዊ የጦር መሳሪያዎችም መታጠቅ ይችላል የተባለ ሲሆን፤ ከአየር ወደ ምድርና ወደ ውሃ የሚወነጨፉ ሚሳዔሎችን የመታጠቅ አቅም አለው
የራዳር ምልክቶችን (ሲግናሎችን)ቀድሞ ማነፍነፍና መጣስ የሚችል ሲሆን፤ የሚሳኤል መተኮሻ ጣቢያዎችን ጨምሮ የጦር መርከቦች፣ የጠላት ትዕዛዝ ጣቢያዎች እና ሌሎች ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውን ኢላማዎችን መለየትና ማረጋገጥ ይችላል።
በተጨማሪም በውጊያ ወቅት ድጋፎችን መስጠት፣ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው የጠላት ኢላማዎች እንዲመቱ አቅጣጫ መጠቆም፣ እንዲሁም የተለያዩ ሚሳዔሎችን ማስወንጨፍ ይችላል።
የቻይናው ቻይና CH-7 ድሮን አቅም ከአሜሪካ ሰራሹ RQ-170 ድሮን በብዙ መልኩ ይበልጣል የተባለ ሲሆን፤ RQ-180 ድሮን ጋር ደግሞ ተቀራራቢ አቅም እንዳላቸውም ይነገራል።