ለመሆኑ ሃይፐርሶኒክ የተባለው የጦር ማሳሪያ ከሌሎች ምን የተለየ ያደርገዋል?
ሩሲያ በቅርቡ ሃይፐርሶኒክ የተባለ እና በጦርነት ውስጥ ለመመከት ከባድ ነው የተባለለትን ሚሳዔል በዩክሬን ጦርነት ላይ በመጠቀም ከዓለም ቀዳሚዋ ሀገር ሆናለች።
እጅግ ፈጣን ነው የተባለለት ሃይፐርሶኒክ ሚሳዔል የትኛውንም የምድር ከፍል በሰዓት ውስጥ መምታት የሚችል መሆኑም ይነገርለታል።
የመጨረሻውን የጦር ቴክኖሎጂ በመጠቀም የተመረተው ሃይፐርሶኒክ ሚሳዔል በጦርነት ውስጥ ለመመከት አሊያም ለማቆም አዳጋች እንደሆነም ነው የተገለፀው።
ሃይፐርሶኒክ ምንድን ነው፤ ሚሳዔሉን ከሌሎች ምን የተለየ ያደርገዋል
“ሃይፐርሶኒክ” የሚለው ቃል ከድምፅ በአምስት እጥፍ የሚፈጥን ማንኛውም ነገር የሚገልጽ ሲሆን፤ በሰዓት 6 ሺህ 174 ኪሎ ሜትር ወይም ከዚያ በላይ የሚበር፤ በሌላ አገላለጽ እጅግ በጣም ፈጣን የሚለውን ለመግለጽ ጥቅም ላይ ይውላል።
በዓለም ላይ ያሉ አብዛኞቹ ባላስቲክ ሚሳዔሎች ከድምፅ በአምስት እጥፍ የሚበልጥ ፍጥነት ያላቸው ሲሆን፤ ሃይፐርሶኒክ ሚሳዔሎችን ለየት የሚያደርጋቸው ግን ከምድር በጣም ርቀው አየር ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ የሚምዘገዘጉ መሆናቸው ነው።
እነዚህ አዳዲሶቹ ሚሳይሎች በሁለት አይነት መልክ የተሰሩ ሲሆን፤ የመጀመሪያው `ሃይፐርሶኒክ ግላይድ ተሸከርካሪ` የሚባልና የጠላትን ራዳር ለማታለል ተለያዩ እጥፋችን በመስራት የሚምዘገዘግ ነው
ሁለተኛው ደግሞ `ሃይፐርሶኒክ ክሩዝ ሚሳይል` (ኤች.ሲ.ኤም) ሲሆን፤ በጣም ፈጣን ባይሆንም ዝቅተኛ በሆነ ፍጥነት ለመብረር የተነደፈ እና ጠላት ራዳር ምላሽ መስጫ የሚሰጠው ጊዜ በጣም ጥቂት መሆኑ ይነገራል።
ሩሲያ ‘ኪንዛል’ የተሰኘ ‘ሃይፐርሶኒክ’ ሚሳዔልን ባሳለፍነው ቅዳሜ እና እሁድ ወደ ዩክሬን ማስወንጨፏን ማስታወቋ ይታወሳል።
ሚሳዔሉ በደቡባዊ ዩክሬን የሚገኙ የሃገሪቱ ጦር የነዳጅ ዴፖዎችን፣ የሚሳኤል እና ሌሎች ጦር መሳሪያዎች ማከማቻ ቦታዎችን ማውደሙም ተነግሯል።