በተመድ የቻይና መልዕክተኛ፤ የአሜሪካ ባለስልጣን ታይዋንን ለመጎብኘት ማቀዳቸው “ነገር ፍለጋ” ነው አሉ
ልዩ መልዕክተኛው የቻይና ሕዝብና መንግስት ግዛታዊ አንድነታቸውን ለማስጠበቅ ይገደዳሉ ብለዋል
የአሜሪካ አፈጉባኤ ታይዋንን እጎበኛለሁ ማለታቸውን ተከትሎ በሩቅ ምስራቅ ውጥረት ነግሷል
የአሜሪካ አፈ ጉባዔ ናንሲ ፔሎሲ ወደ ታይዋን ያደርጉታል የተባለው ጉብኝት ግጭት እንደሚያስነሳ ቻይና ገለጸች።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የቻይና ልዩ መልዕክተኛ በአፈጉባኤዋ የታይዋን ጉዞ ዙሪያ ምላሽ መስጠታቸውን ሲጂቲኤን ዘግቧል። ልዩ መልዕክተኛው ሃንግ ጁን የአፈጉባዔዋ ጉብኝት እጅግ አደገኛ መሆኑን ተናግረዋል።
- የቻይናው ፕሬዝዳት “የታይዋን ጉዳይ በእሳት እንደመጫወት ነው” ሲሉ አሜሪከን አስጠነቀቁ
- የቻይናና አሜሪካ የጦር ጀቶች ወደ ታይዋን የአየር ክልል መጠጋታቸው ስጋትን ፈጥሯል
የናንሲ ፔሎሲ የቻይና ጉብኝት ዕቅድ በሁለቱ ሀገራት መካከል ጸብ የሚያጭርና የሚጋግል እንደሆነ ያነሱት አምባሳደሩ፤ የአንድ ቻይና ፖሊስ ቤጅንግ የማትደራደርበት እንደሆነ አንስተዋል።
ታይዋን የቻይና አንድ አካል መሆኗን የማይቀበል አካል ቀይ መስመሩን የጣሰ እንደሆነም ነው አምባሳደር ሃንግ ጁን የገለጹት።
ቤጅንግ የታይዋንን መገንጠል ክፉኛ እንደምትቃወም በተደጋጋሚ ብታሳውቅም ከአሜሪካ አፈጉባዔ ጉብኝት ጋር ተያይዞ ደግሞ ጉዳዩ እንደ አዲስ ተጋግሏል።
ቻይና ፤በምንም ምክንያት የታይዋንን ነጻ መሆን እንደማትቀበል የገለጹት ዲፕሎማቱ በዚህ ጉዳይ ላይ ከቻይና ብሔራዊ ጥቅም ተጻራሪ መቆም አደገኛ ነው ብለዋል፡።
የአሜሪካ አፈጉባዔ ወደ ታይዋን የሚሄዱ ከሆነ ቻይና እርምጃ እንደምትወስድ አስታውቃለች።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የቻይና ልዩ መልዕክተኛ፤ የአሜሪካ አፈጉባኤዋ ወደ ታይዋን የመጓዛቸው ነገር የማይቀር ከሆነ የቻይና መንግስትና ሕዝብ ሉዓላዊነታቸውንና ግዛታዊ አንድነታቸውን ለማስጠበቅ እንደሚገደዱ ገልጸዋል።
በዚህም መሰረት ቤጅንግ አስፈላጊ እንደሆነ ያመነችበትን እርምጃ ልትወስድ እንደምትችል ዲፕሎማቱ ገልጸዋል።