የቻይናና አሜሪካ የጦር ጀቶች ወደ ታይዋን የአየር ክልል መጠጋታቸው ስጋትን ፈጥሯል
ቻይና እና አሜሪካ በአፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ ጉብኝት ዙሪያ የገቡበት መካረር እየጨመረ ይገኛል
ሶስት የቻይና የጦር ጀቶች አስቀድመው በታይዋን የአየር ክልል ገብተዋል ተብሏል
የቻይና እና አሜሪካ የጦር ጀቶች ወደ ታይዋን የአየር ክልል መጠጋታቸው ስጋትን ፈጥሯል።
የአሜሪካ የተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ናንሲ ፔሎሲ በእስያ ሀገራት ጉብኝታቸው ውስጥ ታይዋንን ማካተታቸው ቻይናን አስቆጥቷል።
ናንሲ ፔሎሲ ታይዋንን የሚጎበኙ ከሆነ ጦሯ “ዝም ብሎ እንደማይቀመጥ” ቻይና ማስጠንቀቋ ይታወሳል።
በታይዋን የሚሰራጭ አንድ ቴሌቪዥን በትዊተር ገጹ ናንሲ ፔሎሲ ነገ ማለዳ ወደ ታይዋን እንደሚመጡ መዘገቡን ተከትሎ የቻይና እና አሜሪካ ውጥረት ጨምሯል።
ዘገባው ከወጣ በኋላም J-16 የተሰኙ አራት የቻይና የጦር አውሮፕላኖች የታይዋንን የአየር ክልል ጥሰው መግባታቸውን አርቲ ዘግቧል።
ይሄንን ተከትሎም የአሜሪካ የጦር አውሮፕላኖች በሌላ አቅጣጫ ወደ ታይዋን እንደቀረቡ ተዘግቧል።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዣኦ ሊጂያን "የአሜሪካ መንግስት ቁጥር 3 ባለስልጣን" እንደመሆናቸው ቻይና የራሴ ግዛት ናት ብላ የምትቆጥራትን ታይዋንን የሚጎበኙ ከሆነ ሁኔታው "ወደ አስከፊ የፖለቲካ ተጽእኖ ያመራል" ብለዋል።
የአሜሪካ አፈጉባዔ ናንሲ ፔሎሲ የእስያ ጉዟቸውን ቅዳሜ እለት መጀመራቸው አይዘነጋም።
የአፈጉባኤዋ የሩቅ ምስራቅ ሀገራት የመጎብኘት ጉዞ ሲንጋፖርን፣ ማሌዥያን ፣ ደቡብ ኮሪያንና ጃፓን እንደሚያካትትም ነበር በወቅቱ የገለጸው።
የጉዟቸው ዓላማ በአሜሪካ እና በሀገራቱ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር የገለጹት ናንሲ ፔሎሲ፤ በእስያ ጉብኝታቸው ታይዋንን እንደሚጎበኙ ቀደም ብለው ገልጸው የነበረ ቢሆንም በአሁኑ የጉዞ ዝርዝር ግን ታይዋን አልጠቀሱም።
አፈጉባዔዋ በጉዞ ታይዋንን ያልጠቀሱት ከቻይና በተሰነዘረ የማስፈራሪያ ዛቻ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።
ናንሲ ፔሎሲ ወደ ታይዋን ከሄዱ ቻይና ታደራዊ እርምጃ እንደምትወስድ ማስጠንቀቋን ተከትሎ ውጥረቱ አይሏል።
ቻይና በታይዋን ጉዳይ እንደማትደራደር በተደጋጋሚ ስትገልጽ አሜሪካ ደግሞ ታይዋንን የሚነካ ብሔራዊ ጥቅሜን የነካ ነው እያለች ነው።
ከሰሞኑ የስልክ ውይይት ያደረጉት የቻይና እና የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች በጭቅጭቅ የተሞላ ውይይት አድርገዋል።
የሁለቱ ፕሬዝዳንቶች የንግግር ርዕስ ታይዋን የነበረች ቢሆንም በተለመደ ያለመስማማት መንፈስ ንግግራቸውን ጨርሰዋል ተብሏል።