የቻይናው ፕሬዝዳት “የታይዋን ጉዳይ በእሳት እንደመጫወት ነው” ሲሉ አሜሪከን አስጠነቀቁ
የቻይና እና የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች በማስጠንቀቅ የታጀበ የስልክ ውይይት አድርገዋል
ፕሬዝዳት ጆ-ባይደን “አሜሪካ ታይዋንን በተመለከተ ያላት ፖሊሲ አልተለወጠም” ብለዋል
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ-ባይደን እና የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ከአራት ወራ በኋላ በስልክ ውይይት አድርገዋል።
በአለመግባባት ውስጥ ያሉት የአሜሪካ እና የቻይና መሪዎች በታይዋን ጉዳይ በመወራረፍና ማስጠንቀቅ የታጀበ ዘለግ ያለ ስልክ ቆይታ ማድረጋቸው መገናኛ ብዙሃን እየዘገቡ ነው።
ፕሬዝዳንት ጆ-ባይደን ሀገራቸው የታይዋንን የህልውና ጥያቄን የሚቀይር የተናጠል እርምጃን አጥብቃ እንደምትቃወም ለቻይናው አቻቸው ዢ ዢንፒንግ ግልጽ አድርገዋል።
አሜሪካ ታይዋንን በተመለከተ ያላት ፖሊስ “አልተለወጠም” ሲሉም አስረግጠዋው ተናግረዋል ፕሬዝዳንቱ፡፡
ባይደን “የአንድ ቻይናን መርህ” እንዲያከብሩ ያሳሰቡት የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ በበኩላቸው፤ የታይዋን ጉዳይ በእሳት እንደመጫወት ነው ሲሉም ማስጠንቀቂያ አዘል መልእክት አስተላልፈዋል።
“ማንኛውም በእሳት የሚጫወት መቃጠሉ አይቀርም” ሲሉ ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ጆ ባይደንን ወርፈዋል።
ሁለቱ መሪዎች በውይይታቸው አሜሪካ በቻይና ምርቶች ላይ ስለጣለችው ቀረጥ ግን ምን ሃሳብ አልተለወለወቱም ተብሏል።
አሜሪካ እና ቻይና በታይዋን ጉዳይ ቅራኔ ውስጥ ከገቡ የቆዩ ቢሆንም፤ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየተስተዋለ ያለው ፍጥጫ ግን ምናልባትም ሀገራቱ ወደለየለት ግጭት እንዳይገቡ የሚያስጋ እንደሆነ በርካቶች ይገልጻሉ፡፡
በተለይም የአሜሪካዋ አፈ ጉባዔ ናንሲ ፔሎሲ ከቀናት በፊት ታይዋንን ሊጎበኙ እንሚችሉ ማናገራቸው ተከትሎ በሁለቱ ሀገራት መካከል አዲስ አለመግባባት መከሰቱ የሚታወቅ ነው፡፡
ናንሲ ፔሎሲ እቅድ ን ተከትሎ የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዛኦ ሊጃን “ናንሲ ፔሎሲ ታይዋንን የሚጎበኙ ከሆነ ቻይና ወታደራዊ እርምጃዎችን ጨምሮ ማንኛውንን አይነት እርምጃ ለመውሰድ በሚገባ ተዘጋጅታለች” ብለዋል፡፡
"አሜሪካ አሁን በያዘችው እቅድ የምትመራ ከሆነም ቻይና ጠንካራ እርምጃ መውሰዷን ትቀጥላለች ፣ለሚፈጠረው ክስተትም አሜሪካ ሃላፊነቱን ትወስዳለች” ሱሉም ቃል አቀባዩ አክለዋል፡፡
እናም የአሁን የፕሬዝዳንት ጀ-ባይደን እና ፕሬዝዳንት ዢ የስልክ ላይ ቃላት መወራወር ታይዋንን እንደምክንያት በማድረግ በሀገራቱ መካከል የሰፈነውን ውጥረት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ለመድረሱ ሁነኛ ማሳያ ነው ተብሏል፡፡
ቻይና ታይዋን የግዛቴ አንድ አካል እንጂ ሀገር አይደለችም በሚል ጠንካራ አቋም ያላት ሲሆን ታይዋን ይሄንን እንድትቀበል የተለያዩ ጫናዎችን በማድረስ ላይ እንደሆነች ይጠቀሳል፡፡
የታይዋን መንግስት በበኩሉ ጉዳዩ የ23 ሚሊዮን ዜጎች ውሳኔ እንጂ የቻይና ማዕከላዊ መንግስት አይደለም በሀይል ከተጠቃንም ሁላችንም ለሉዓላዊነታችን እንዋጋለን ስትል ትደመጣለች፡፡