ሰሜን ኮሪያ በጃፓን አየር ክልል ላይ ሚሳዔል ስታስወነጭፍ ከ5 ዓመት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው
ኒውክሌር ታጣቂ ሀገር የሆነችው ሰሜን ኮሪያ በጃፓን የአየር ክልል በኩል አዲስ የባላስቲክ ሚሳዔል ወደ ፓሲፊክ ውቂያኖስ መተኮሷ ተሰምቷል።
ሀገሪቱ ትናንት ያካሄደችውን የባላስቲክ ሚሳዔል የማስወንጨፍ ሙከራ ጨምሮ ባለፉት 10 ቀናት ውስጥ ለአምስተኛ ጊዜ የተካሄደ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል።
ሰሜን ኮሪያ በጃፓን ሰማይ ላይ ያስወነጨፈችው የባላስቲክ ሚሳዔልን የጃፓን የባህር ድንበር ጠባቂዎች እና የደቡብ ኮሪያ የጥምር ጦር አዛዥ ቀድመው እንደለዩት አስታውቀዋል።
ይህንን ተከትሎም ለጃፓናውያን መጠለያዎች ውስጥ እንዲሸሸጉ የጥንቃቄ መልእክት እንዲደርሳቸው መደረጉ ተነግሯል።
እንዲሁም የባላስቲክ ሚሳዔሉ ጃፓንን እስኪያልፍ ድረስ በሰሜን ምስራቅ ጃፓን በሚገኙት ሆካይዶ እና ኦሞሪ ክልሎች የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት በጊዜያዊነት እንሰዲቆም ተደርጎ ነበር።
ሰሜን ኮሪያ በጃፓን አየር ክልል ላይ ሚሳዔል ስታስወነጭፍ ከፈረንጆቹ 2017 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ታውቋል።
የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚዮ ኪሺዳ፤ የሰሜን ኮሪያን ተግባር ያወገዙ ሲሆን፤ ተግባሩንም “አረመኔያዊ ድርጊት” ሲሉ ኮንነውታል።
የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ሱክ ዬዎል በበኩላቸው፤ የሰሜን ኮሪያ የባላሲቲክ ሚሳዔል መተኮስን ተከትሎ ከባድ ምላሽ ሊሰጥ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
ሰሜን ኮሪያ ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ በተከታታይ የሚሳዔል ማስወንጨፍ ሙከራዎችን እያደረገች እንደሆን ይታወቃል።
ፒዮንግ ያንግ ባሳለፍነው ሳምንት በደቡብ ኮሪያ ጉብኝት ላይ የነበሩት የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሀሪስ ሴኡልን ለቀው ከወጡ ከሰዓታት በኋላ ሚሳዔሎችን መተኮሷ ይታወሳል።