ሩሲያ “አሜሪካ የሰሜን ኮሪያን ትዕግስት እየተፈታተነች ነው” ስትል ከሰሰች
ሩሲያ በተለያዩ መድረኮች ለሰሜን ኮሪያ ያለትን አጋርነት በማሳየት የምትታወቅ ሀገር ናት
ሞስኮ በኮሪያ ልሳነ ምድር ላለው ውጥረት ዋሽንግተንን ተጠያቂ ታደርጋለች
ፒዮንግያንግ በጃፓን አቅራቢያ ያረፈ አህጉር አቋራጭ ባሊስቲክ ሚሳዔል ከተኮሰች በኋላ አሜሪካ የሞስኮን ጥብቅ አጋር የሆነችውን ሰሜን ኮሪያን ትዕግስት እየፈተነች መሆኑን ሩሲያ ተናግራለች።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር ሰርጌይ ሪያብኮቭ ለመንግስታዊው ሪያ የዜና ወኪል፤ ሞስኮ በኮሪያ ልሳነ ምድር የነገሰውን ውጥረት ለመፍታት ዲፕሎማሲያዊ አካሄድን ብትመርጥም የአሜሪካና አጋሮቿ አካሄድ አደገኛ የሚባል መሆኑን ገልጸዋል።
- አሜሪካ የሰሜን ኮሪያን የኒውክር ሙከራ የማስቆም አቅም ያላቸው ሩሲያ እና ቻይና ናቸው አለች
- ሰሜን ኮሪያ አሜሪካ ላይ “ከባድ ወታደራዊ እርምጃ እወስዳለሁ” በማለት ዛተች
“በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አሜሪካ እና በአካባቢው ያሉ አጋሮቿ የተለየ መንገድ እንደሚከተሉ በግልጽ እየታየ ነው"ሲሉም ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስተሩ ተናግረዋል።
አክለውም "የፒዮንግያንግ ትዕግስት እየተፈተነ ያለ ይመስላል" ብለዋል።
ሩሲያ በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ሳይቀር አሜሪካና አጋሮቿ በሰሜን ኮሪያ ላይ እየፈጠሩት ያለውን ጫና ትክክል እንዳልሆነ በመሞገት ለፒዮንጊያንግ ያላት አጋርነት ስትገልጽ የምትታይ ሀገር ናት።
በቅርቡ በሰሜን ኮሪያ ጉዳይ በተሰበሰበው የጸጥታው ምክር ቤት የተንጸባረቀው የሩሲያ ኃሳብ አሜሪካ እና አጋሮቿን ያስደነገጠ እንደነበር አይዘነጋም።
አሜሪካ እና አጋሮቿ የሰሜን ኮሪያ የቅርብ ጊዜያት ድርጊት የኮሪያ ልሳነ ምድርን የሚያተራምስ በመሆኑ ሃይ ሊባል ይገባል የሚል ክስ ቢያቀረቡም ሩሲያ በበኩሏ በኮሪያ ምድር ላለው ውጥረት ተጠያቂዋ አሜሪካ ራሷ ናት ስትል ተደምጣለች።
የሩስያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምክትል አምባሳደር አና ኢቭስቲኒቫ በኮሪያ ልሳነ ምድር ላይ ለደረሰው የከፋ ሁኔታ አሜሪካ ተጠያቂ ናት ሲሉ መልሰዋል።
ለውጥረቱ “ዋሽንግተን የፒዮንግያንግን ማዕቀብ በመጠቀም እና ጫና በመፍጠር በአንድ ወገን ትጥቅ እንድትፈታ የማስገደድ ፍላጎት” ነው ሲሉም አሜሪካን ወቅሰዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰሜን ኮሪያ አሜሪካ ትንኮሳዋን የማታቆም ከሆነ የኃይል እርምጃ ለመውሰድ እንደምትገደድ ከቀናት በፊት ማስጠንቀቋ አይዘነጋም።
ፒዮንጊያንግ ባለችው መሰረት የአጭር ርቀት ባለስቲክ ሚሳዔል ማስወንጨፏን ደቡብ ኮሪያ በትናንተናው እለት ገልጻለች።
ሚሳዔሉ ወንሳን ከተሰኘችው የሀገሪቱ ምስራቃዊ የባህር ዳርቻ ወደ ባህር እንደተወነጨፈም ነው የደቡብ ኮሪያ መከላከያ ሚኒስቴር ያስታወቀው።
ፒዮንግያንግ የሚሳዔል ሙከራ ያደረገችው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ቾይ ሰን ሁይ አሜሪካን ያስጠነቀቁበትን መግለጫ ካወጡ ከጥቂት ስአት በኋላ ነው።
የሰሜን ኮሪያ እርምጃ በዚህ አላበቃም በዛሬው እለትም አሜሪካ መድረስ ሚችል ነው የተባለለት አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳዔል ወደ ጃፓን አህጉር ማስወንጨፏ ተሰምቷል።