ሆንግ ኮንግ ከቻይና ጋር ከተቀላቀለች 25 ዓመት ሆኗታል
የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂን ፒንግ በአዲስ የጸጥታ ሕግ ምክንያት ተቃውሞ ላይ የነበረችውን ሆንግ ኮንግን ሊጎበኙ መሆኑ ተነግሯል።
ፕሬዝዳንቱ በጉብኝታቸው ሆንግ ኮንግ ከቻይና ጋር የተቀላቀለችበትን 25 ዓመት ክብረ በዓል እንደሚታደሙም ይጠበቃል።
ፕሬዝዳንቱ ከዋናው የቻይና ግዛት (በልዩ አስተዳደር ውስጥ ካሉት ) ውጭ ጉብኝት ሲያደርጉ ከ2020 ወዲህ የመጀመሪያቸው መሆኑ ተገልጿል። ጉብኝታቸው ከሀገራቸው እንደተነሳ ከተገለጸው የኮሮና ወረርሽን በኋላ የሚደረግ መሆኑንም ነው ሽንዋ የዘገበው።
ፕሬዝዳንቱ በሃምሌ ወር መጀመሪያ በሚካሄደው የሆንግ ኮንግ ልዩ አስተዳደር ግዛት የመንግስት መስረታ ላይ እንደሚገኙም ነው የሚጠበቀው።
ጆን ሊ የከተማዋ አዲስ አስተዳዳሪ በመሆን እንደሚሾሙም ይጠበቃል። ሃምሌ አንድ ቀን 2022 ስልጣን የሚያስረክቡት ካሬይ ላም ወደ ስልጣን ሲመጡ ፕሬዝዳንቱ በቦታው ተገኝተው እንደነበር ይታወሳል።
ተሰናባቿ የሆንግ ኮንግ አስተዳዳሪ በስልጣን ዘመናቸው ከፍተኛ ተቃውሞ ማስተናገዳቸው ይታወሳል።
የቻይና መንግስት፤ የሆንግ ኮንግ ግዛት በርካታ የጸጥታ ችግሮች እየተስተዋሉበት እንደሆነ በመግለጽ አዲስ የጸጥታ ሕግ ማውጣቱ የሚታወስ ሲሆን፤ ይህም በርካቶችን ለተቃውሞ አሰባስቦ ነበር።
ሕጉ ሆንግ ኮንግን ከቻይና ስለመገንጠል፣ ሀገር ክህደትንና ሽብርተኝነትን ለመከላከልና ለማውገዝ ያለመ ብሎም በሆንግ ኮንግ ጉዳይ የውጭ ጣልቃ ገብነትን ለመመከትም ያለመ እንደነበር ቤጅንግ ስትገልጽ ቆይታለች።
ብሪታኒያ ሆንግ ኮንግን በሊዝ ገዝታ ጃፓን እንድታስተዳድርላት ያስተላለፈች ቢሆንም፤ ጃፖን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በመሸነፏ ብሪታኒያ ሆንግ ኮንግን በድጋሚ ማስተዳደር ጀምራ ነበር።
ብሪታኒያ ለ 99 ዓመታት በሊዝ ስታስተዳድራት የነበረችው ሆንግ ኮንግ ከቻይና ጋር የተቀላቀለችው ከ25 ዓመታት በፊት ነበር።