አሜሪካ ከሰሞኑ ለሩሲያ ድጋፍ አድርገዋል በሚል በቻይና ኩባንያዎች ላይ ተመሳሳይ ማዕቀብ ጥላለች
ቻይና በ12 የአሜሪካ ኩባንያዎች ላይ ማዕቀብ ጣለች።
የዓለማችን ቁጥር አንድ እና ሁለት ልዕለ ሀያል ሀገራት አሜሪካ እና ቻይና አንዳቸው በሌላቸው ላይ ማዕቀብ እየጣሉ ይገኛሉ።
ከሰሞኑ አሜሪካ በቻይና ኩባንያዎች ላይ ማዕቀብ የጣለች ሲሆን ምክንያቱ ደግሞ ለሩሲያ ድጋፍ አድርገዋል በሚል ነው።
ቻይናም 12 የአሜሪካ ጦር መሳሪያ አምራች ኩባንያዎች ላይ ማዕቀብ በመጣል በዋሽንግተን ለተደረገባት ቅጣት የአጸፋ እርምጃ መውሰዷን አስታውቃለች።
እንደ ሮይተርስ ዘገባ ቻይና ዋነኛ የአሜሪካ ጦር መሳሪያ አምራች ኩባንያዎች ለታይዋን ድጋፍ አድርገዋል በሚል ማዕቀብ ጥላለች።
ኩባንያዎቹ በተጣለባቸው ማዕቀብ ምክንያት በቻይና ያላቸው ሀብት እንዳይንቀሳቀስ፣ የኩባንያዎቹ አመራሮች ቻይናን እንዳይጎበኙ እና ከቻይናዊያን ጋር ግብይት እንዳይፈጽሙ ታግደዋል።
በቻይና ማዕቀብ ከተቀጡ የአሜሪካ ጦር መሳሪያ እምራች ኩባንያዎች መካከል ሎክሂድ ማርቲን፣ ጀነራል ዳይናሚክስ እና ራይቲዮን ዋነኞቹ ናቸው።
የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በዩክሬን ጦርነት ገለልተኛ መሆኑን በአንጻሩ አሜሪካ ግን ፍጹም ለዩክሬን እየደገፈች እንደሆነ ይህም ዘላቂ ሰላም እንደማያመጣ አስታውቋል።