ኢትዮጵያ በአዲስ አበባ የሚገኙት የአሜሪካ አምባሳደር ያደረጉትን ንግግር ተቃወመች
አምባሳደር ኢርቪን ማሲንጋ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ያነሷቸው ወቀሳዎች በተሳሳቱ መረጃዎች ላይ የተመሰረተ ነው ብሏል የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
አምባሳደሩ በኢትዮጵያ የንጹሃን ግድያ፣ ያለህጋዊ አግባብ የሚፈጸም እስርና ስወራ በአፋጣኝ እንዲቆም ማሳሰባቸው ይታወሳል
ኢትዮጵያ በአዲስ አበባ የሚገኙት የአሜሪካ አምባሳደር ያደረጉትን ንግግር ተቃወመች።
አምባሳደር ኢርቪን ማሲንጋ ትናንት በአሜሪካ ግቢ ባደረጉት “የሰብአዊ መብትና ምክክር የፖሊስ ንግግር” ያነሷቸው ወቀሳዎች በሀሰተኛ መረጃ የተመሰረተ ነው ብሏል የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ።
አምባሳደር ኢርቪን “ኢትዮጵያ ሳትጠይቃቸው የውስጥ ችግሯን እንዴት ትፍታው የሚል ምክርን ሲለግሱ ታይተዋል” የሚለው መግለጫው፥ በምርጫ ስልጣን ላይ ያለውን የኢትዮጵያ መንግስት ንጹሃንን ከሚያግቱና ከሚያሸብሩ አካላት ጋር መጥቀሳቸውም ተገቢ አለመሆኑን አብራርቷል።
አምባሳደሩ በንግግራቸው ያነሷቸው ጉዳዮች እና ወቀሳዎች በሀገሪቱ ሁኔታ በቂ ግንዛቤ እንደሌላቸው ያሳያል በሚልም ተቃውሞውን ገልጿል።
በኢትጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኢርቪን ማሲንጋ መርካቶ አካባቢ በሚገኘው የአሜሪካ ግቢ ያደረጉት የ10 ደቂቃ ንግግር በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ፣ ግጭቶችና የሰብአዊ መብት አያያዝና ሁሉን አካታች ሀገራዊ ምክክር ዙሪያ ትኩረት ያደርጋል።
አምባሳደሩ በንግግራቸው ሁሉም የግጭት ተዋናዮች ንጹሃንን ለስቃይና መፈናቀል እየዳረጉ መሆኑን በመጥቀስ እንደ ትምህርቤት፣ የህክምና ተቋማት፣ የውሃና ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎት መስጫ መሰረተ ልማቶችን ኢላማ ያደረገ ጥቃት እንዳይፈጽሙ አሳስበዋል።
የንጹሃን ግድያ፣ ያለህጋዊ አግባብ የሚፈጸም እስርና መሰወር እንዲሁም ከግጭቶች ጋር የተያያዙ አስገድዶ መድፈር መበራከት በአፋጣኝ እንዲቆምና በሽግግር ፍትህ አጥፊዎች ተጠያቂ እንዲሆኑም ጥሪ አቅርበዋል።
የታጠቁ ሃይሎች ፖለቲካዊ ፍላጎታቸውን በንግግር ከመፍታት ይልቅ ጦር መስበቃቸውና መንግስት ይህን ለማስቆም የሚወስዳቸው እርምጃዎች መጠንከር የውይይት በሩን እየዘጋው እንዳይሄድ ስጋት አለኝ ሲሉም ተደምጠዋል።
በአማራ እና ኦሮሚያ ክልል የሚገኙ የታጠቁ ሃይሎች ልዩነቶችን በሰላማዊ ንግግር እንዲፈጡ የጠየቁት አምባሳደር ኢርቪን ማሲንጋ፥ ህወሃትም ከአማራ ክልል ጋር የሚዛገብባቸውን አካባቢዎች ጉዳይ በንግግር ብቻ ይፈታ ዘንድ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
ግጭቶች ቆመው ሁሉን አካታች ብሄራዊ ምክክር ለመጀመር እንዲቻልም ሀገርአቀፍ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም እንዲደረግና የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱም ነው የጠየቁት።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአምባሳደሩ የተነሱ ወቀሳዎች “ከታሪካዊው የኢትዮጵያ እና አሜሪካ ግንኙነት የሚቃረን” ነው ብሏል።
ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር በሰላምና ደህንነት፣ በሰብአዊ መብት አያያዝ እና ዴሞክራሲን ማጎልበት በሚያስችሉና ሌሎች ጉዳዮች ለመምከርና በትብብር ለመስራት ሁሌም በሯ ክፍት መሆኑንም መግለጫው ጠቁሟል።
ሚኒስቴሩ አምባሳደሩ አንስተዋቸዋል ያሏቸውን “ሀሰተኛ ወቀሳዎች” እንዲታረሙ በአዲስ አበባ ከሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ጋር እንደሚሰራም ነው ያነሳው።