ቻይና በአምስት የአሜሪካ ጦር መሳሪያ አምራች ኩባንያዎች ላይ ማዕቀብ ጣለች
ማዕቀብ የተጣለባቸው ኩባንያዎች ለታይዋን የጦር መሳሪያ የሸጡ ናቸው ተብሏል
ታይዋን በማንኛውም መንገድ ወደ ቻይና መዋሀዷ አይቀሬ ነው ተብሏል
ቻይና በአምስት የአሜሪካ ጦር መሳሪያ አምራች ኩባንያዎች ላይ ማዕቀብ ጣለች።
የዓለማችን ሁለተኛዋ ባለግዙፍ ኢኮኖሚ ቻይና በአምስት የአሜሪካ ጦር መሳሪያ አምራች ኩባንያዎች ላይ ማዕቀብ ጥላለች።
ቤጂንግ በኩባንያዎቹ ላይ ማዕቀብ የጣለችው የግዛቴ አንድ አካል ናት ብላ ለምታምናት ታይዋን የጦር መሳሪያ ሸጠዋል በሚል ነው።
ማዕቀብ ከተጣለባቸው የጦር መሳሪያ ፋብሪካዎች መካከልም ቢኤኢ ሲስተም፣ አሊያንት ቴክኖ ሲስተም፣ ኤሮቪሮንመንት፣ ቪያ ሳት እና ዳታ ሊንክ ዋነኞቹ ናቸው።
ኩባንያዎቹ በቻይና ያላቸው ሀብት እንዳይንቀሳቀስ እና ከቻይናዊያን ጋር ምንም አይነት የንግድ ስምምነት እንዳይኖራቸው የሚያደርግ እንደሆነ ሮይተርስ ዘግቧል።
አሜሪካ ከፈረንጆቹ 1979 ጀምሮ ግንኙነቷን ከታይዋን ወደ ቻይና በይፋ ያዞረች ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ከታይዋን ጋር ያላትን ወዳጅነት እያጠናከረች ትገኛለች።
በአንጻሩ ዋሽንግተን ከቤጂንግ ጋር ያላት ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸረ ሲሆን ይህም ሆን ተብሎ እንደሚካሄድ የቻይና ውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ማዕቀቡን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ላይ አስታውቋል።
ሚንስቴር አክሎም ቻይና የግዛቷን አንድነት እና ሉዓላዊነቷን ለማስጠበቅ ሁሌም ዝግጁ መሆኗን ገልጾ የታይዋን ጉዳይም በማንኛውም መንገድ መዋሀዷ አይቀሬ ነው ብሏል።
ሉዓላዊ ሀገር ነኝ የምትለው ታይዋን ከአንድ ሳምንት በኋላ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የምታካሂድ ሲሆን ምርጫውን እንደሚያሸንፉ የተገመቱት እጩ ከቻይና ጋር ያላቸውን ግንኙነት ሙሉ ለሙሉ ሊያበላሹ እንደሚችሉ ተሰግቷል።
አዲስ የሚመረጠው ፕሬዝዳንት ታይዋን ሀገር መሆኗን ሊያውጅ ይችላል በሚል የተሰጋ ሲሆን ይህ ከሆነ ቻይና ይህን ለማስቆም በምትወስደው እርምጃ ከአሜሪካ ጋር የቀጥታ ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላልም ተብሏል።
ቻይና ታይዋንን ከዚህ ድርጊት ለመጠበቅ በሚል ተደጋጋሚ የጦር ቅኝት በማድረግ ላይ ትገኛለች።