ከአሜሪካዋ አፈጉባኤ ፔሎሲ የታይዋን ጉብኝት በኋላ ቻይና እና ታይዋን ወታራዊ ፍጥጫ ውስጥ ገብተዋል
የአሜሪካ አፈጉባዔ ናንሲ ፔሎሲ ሀገራቸው ለታይዋን እያደረገች ያለውን ድጋፍ እንደማታቋርጥ አስታወቁ።
ታይዋንን የጎበኙት ፔሎሲ ዋሸንግተን ታይዋንን ለመደገፍ ያሳየችውን ቁርጠኝነት እንደማትተው ገልጸዋል።
ትናንት ምሽት ላይ ታይፒ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የታይዋን ሹሞች አቀባበል አድርገውላቸው ነበር። ከአውሮፕላን ማረፊያ ከወጡ በኋላም ውይይት ማድረጋቸውና ሽልማት መቀበላቸው ተጠቅሷል።
አፈጉባዔዋ ከታይዋን ሽልማት የተበረከተላቸው የታይዋንንና የዋሽንግተንን ወዳጅነት እንዲጠናከር ስላደረጉ ነው ተብሏል።
ፔሎሲ ሀገራቸው ከታይዋን ጋር ወዳጅ በመሆኗ እንደሚኮሩም ተናግረዋል።አሜሪካ ይህንን የታይዋንን ወዳጅነት መቸም እንደማትተውና እንደማትከዳም አፈጉባዔዋ አስታውቀዋል።
ቻይናን ባስቆጣው ጉዟቸው ደስተኛ መሆናቸውን ፔሎሲ ቢገልጹም ዓለም ግን ተጨማሪ ውጊያ እንዳይመጣ ሰግቷል።
ቤጅንግ፤ ታይዋንን ከቻይና ጋር የመቀላቀሉ ሂደት አይቀሬ መሆኑን ገልጻለች።የታይዋን ባለስልጣናት የአሁን ድርጊት ግዛቲቱን ቀውስ ውስጥ ይከታታል ስትል ቻይና አስጠንቅቃለች።
ቤጅንግ ተገንጣይ ባለቻቸው ሁለት የታይዋን የድጋፍ ሰጭ ድርጅቶች ላይ ማዕቀብ መጣሏን አስታውቃለች።ከዚህ ባለፈም ቻይና ከታይዋን በሚገባ ፍራፍሬ ላይም ማዕቀብ ጥላለች።
ናንሲ ፔሎሲ ወደ ታይዋን መጓዛቸውን ተከትሎ የቻይ የጦር አውሮፕላኖች የታይዋንን የአየር ክልል ጥሰው መግባታቸው ተዘግቦ ነበር።