አዲሱ አምባሳደር የአሜሪካ እና ቻይና ወዳጅነትን ማሻሻል ዋነኛ ስራቸው ይሆናል ተብሏል
ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን ሴኔቱ ኒኮላስ በርንስን በቻይና የአሜሪካ አምባሰደር አድርጎ እንዲሾምላቸው በእጩነት አቅርበዋል።
ኒኮላስ በርንስ በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ጆርጅ ደብሊው ቡሽ የስልጣን ዘመን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ስር ሶስተኛው ከፍተኛ ባለስልክጣን ነበሩ።አሜሪካ ከቻይና ጋር በንግድ ጦርነት፤በታይዋን ጉዳይ፤በቴክኖሎጂ፤በደቡባዊ ቻይና ባህር እና በሌሎች ወታደራዊ ጉዳዮች ያላቸው አለመግባባት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ይገኛል።
የሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በተለይም በፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ የስልጣን ዘመን ወደ ከፋ ደረጃ ደርሶ በርካታ ተጨማሪ ማዕቀቦች ተጥለዋል።
የአሁኑ ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን ወደ ስልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ የሁለቱ ሀገራት ወዳጅነት ይሻሻላል ቢባልም አዲስ ነገር አለመታየቱን ሮይተርስ ዘግቧል።ፕሬዘዳንቱ ግንኙነቱን ለማሻሻል አንጋፋ ዲፕሎማት የተባሉት ኒኮላስ በርንስ አዲሱ በአሜሪካ የቻይና አምባሳደር ተደርገው ለመሾም ማቀዳቸው ዘገባው አክሏል።
ፕሬዘዳንቱ ሀገራቸው ከቻይና ጋር ወዳጅነታቸውን ለማሻሻል ፖለቲከኛ ሳይሆን ሀገሪቱን በደንብ የሚያውቅ ጉምቱ ዲፕሎማት መሾም መፈለጋቸው ኒኮላስ በርንስን እንዲያጩ አደርጓቸዋል ተብሏል።
ኒኮላስ በርንስ በተለይም የቻይናን ፖለቲካ፤ባህል፤ አካባቢያዊ ሁኔታ እና ሌሎች አስፈላጊ ጉዳዮችን ያውቃሉ መባሉ ለሹመቱ ትክክለኛው እጩ በመሆናቸው የአሜሪካ ሴኔት የአምባሳደሩን ሹመት እንዲያጸድቅላቸው ፕሬዘዳንቱ ጠይቀዋል።
ኒኮላስ በርንስ በፈረንጆቹ ከ2005 እስከ 2008 ዓመት ድረስ በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፖለቲካ ጉዳዮች ሀላፊ በመሆን አገልግለዋል።ኒኮላስ በርንስ በሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ወይም ኔቶ የአሜሪካ አምባሳደር እና በግሪክ የአሜሪካ አምባሳደር በመሆንም እንዳገለገሉም በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ የስልጣን ዘመን ቴሪ ብራንስታድን በቻይና የአሜሪካ አምባሳደር ተደርገው ቢሾሙም በቅርቡ ተነስተዋል።