ሩሲያ፤ ቻይና በዩክሬን ዙሪያ ያቀረበችውን ምክረ-ሃሳብ ለመቀበል"ጊዜው አሁን አይደለም" አለች
ሞስኮ፤ ግጭቱ እልባት የሚያገኘው በአራቱም የዩክሬን ግዛቶች ላይ ያለኝን ጥያቄ እውቅና ሲያገኝ ነው ብላለች
ቻይና፤ የዩክሬን ቀውስ ሊቆም የሚችለው "ፖለቲካዊ መፍትሄ" በማበጀት ነው ትላለች
በዩክሬን እየተካሄደ ባለው ጦርነት ራሷን ገለልተኛ አድርጋ የምትቆጥረው ቻይና፤ ከተጀመረ ድፍን አንድ አመት የሆነውን ደም አፋሳሽ ጦርነት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ሁለቱን ወገኖች ለማሳመን ያላትን ቁርጠኛነት ያሳወቀቸው ባሳለፍነው ሳምንት ነበር፡፡
ቻይና በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቷ በኩል ባወጣችው ባለ 12 ነጥብ ሰነድ እንደሚያመላክተው ከሆነም የዩክሬን ቀውስ ሊቆም የሚችለው "ፖለቲካዊ መፍትሄ" በማበጀት ነው፡፡
ቤጂንግ "ጦርነቱ መቆም አለበት፤ የዩክሬን ቀውስ ከቁጥጥር ውጭ መሆን የለበትም" የሚል አቋሟ ባንጸባረቀችበት ጽሁፏ፤ የሁለቱም ሀገራት ሉዓላዊነት መከበር ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ እንዳልሆነም ገልጻለች፡፡
ዘላቂ ሰላም የሚመጣው የሞስኮ ጦር ዩክሬንን ለቆ ሲወጣ እንደሆነም ጭምር ገልጻለች ቻይና፡፡
ቤጂንግ ይህን ትበል እንጅ የቤጂንግ እቅድ በክሬምሊን ባለስልጣናት በኩል ተቀባይነት ያገኘ አይመስልም፡፡
ሩሲያ፤ ለዩክሬን ቀውስ "ፖለቲካዊ መፍትሄ" ለማበጀት በቻይና በኩል የቀረበውን ምክረ-ሃሳብ አሁን መቀበል እንደማትችል አስታወቀች፡፡
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ እንደተናገሩት "ቻይናውያን ጓደኞቻችን ያቀረቡትን የመፍትሄ እቅድ ትኩረት ሰጥተን አይተነዋል" ነገር ግን ሰላም ለማምጣት የተቀመጡ ሁኔታዎች ለመቀበል እንቸገራለን ብለዋል፡፡
የቻይናን ጥረት ያመሰገነው የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ “ግጭት እልባት ሊያገኝ የሚችለው ሩሲያ በአራት የዩክሬን ክልሎች ላይ ያላትን ጥያቄ እውቅና ሲሰጠው ነው” ብሏል፡፡
ሩሲያ የዶኔትስክ፣ ሉጋንስክ፣ ዛፖሪዝሂያ እና ኬርሰን ክልሎችን ጠቅሊያለሁ ብትልም ሙሉ በሙሉ እንዳልተቆጣጠረቻቸው ይነገራል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ በቅርቡ ዩክሬን ከቻይና ጋር መስራት አለባት በማለት በዩክሬን ጉዳይ ገለልተኛ ነኝ ለምትለው ቤጂንግ ያላቸውን መልካም የሚባል አመለካከት ማንጸባረቃቸው ይታወሳል፡፡
ቻይና "ለግዛታችን አንድነት እና የጸጥታ ጉዳዮች መከበር ጥሩ እይታ ያላት መስለኛል" ሲሉም ነበር የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ ።ያም ሆኖ ቤጂንግ ያቀረበችውን የሰላም እቅድ በምዕራባውያኑ የተወደደ አይመስልም፡፡
ቻይናን ቀንደኛ የሩሲያ አጋር አድርገው ሲከሱ የሚደመጡት አሜሪካ እና አጋሮቿ ቻይና ሰው አልባ አውሮኘላኖችን ጨምሮ ወታደራዊ ድጋፍ ለሞስኮ እያቀረበች ነው እያሉ ነው፡፡
የአሜራካው የስለላ ድርጅት / ሲአይኤ/ ዳይሬክተር ዊሊያም በርንስ ፤ እርግጠኛ መሆን ባይቻልም ቤጂንግ ለሩሲያ ወታደራዊ ዕርዳታ ለማቅረብ እያሰበች መሆኑ ደርሰንበታል ብለዋል፡፡
የዩክሬን ቀውስ አሁንም ድረስ መፍትሄ ያልተበጀለት የዓለም አቀፉ ማህበረስብ ቀዳሚ አጀንዳ ሆኖ እንደቀጠለ ነው፡፡