አሜሪካ ብቻዋን 44 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው የጦር መሳሪያ ወደ ዩክሬን ልካለች
ለጥቂት ሳምንታት ተብሎ የተጀመረው የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት አንድ ዓመት አልፎታል።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ከሩሲያ ጦር እየደረሰባቸው ያለውን ጥቃት ለማስቆም ምዕራባዊያን ተጨማሪ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ እንዲሰጧቸው በመወትወት ላይ ናቸው።
እነዚህ ሀገራትም ለዩክሬን የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን በመስጠት ላይ ሲሆኑ ዩክሬን ግን ድጋፉ በቂ እንዳልሆነ በመናገር ላይ ትገኛለች።
ለዩክሬን በገፍ የጦር መሳሪያ እየሰጡ ካሉ ሀገራት መካከልም አሜሪካ ዋነኛዋ ሀገር እንደሆነች ዩሮ ኒውስ ዘግቧል።
አሜሪካ ብቻዋን እስካሁን 44 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው የጦር መሳሪያ ለዩክሬን የሰጠች ሲሆን ድጋፉ እንደሚቀጥል ይጠበቃል።
ከአሜሪካ በመቀጠልም ብሪታንያ ለዩክሬን ብዙ የጦር መሳሪያ የለገሰች ሲሆን እስካሁን 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጓ ተገልጿል።
ጀርመን እና ፖላንድ ደግሞ እያንዳንዳቸው 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው የጦር መሳሪያ ለግሰዋል ተብሏል።
ሌሎች የምስራቅ አውሮፓ ሀገራት ደግሞ ከዓመታዊ ምርት ድርሻቸው ላይ ከአንድ በመቶ በላይ ለዩክሬን መለገሳቸው ተገልጿል።
ይሁንና ዩክሬን አሁንም የተሰጣት የጦር መሳሪያ በቂ አለመሆኑን የገለጸች ሲሆን በተለይም የጦር ጀት እንዲሰጣት በመወትወት ላይ ትገኛለች።
ሩሲያ በበኩሏ የምዕራባዊያን የጦር መሳሪያ ድጋፍ ጦርነቱን ከማራዘም ውጪ የሚፈይደው ነገር የለም ብላለች።
በአራት የውጊያ ግምባሮች ከሩሲያ ጋር እየተዋጋች ያለችው ዩክሬን በበኩሏ ከምስራቃዊ ግምባር ጦሯ እና ነዋሪዎች ከከተሞች እንዲለቁ አዛለች።