አሜሪካ እና የታሊባን ተወካዮች ለውይይት ቢቀመጡም ልዩነቶች ግን ነበሯቸው ተብሏል
የአሜሪካ ባለስልጣናት ውይይት ያደረጉት በአፍጋኒስታን ማዕከላዊ ባንክ ተቀማጭ ገንዘብ ዙሪያ መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡
በአፍጋኒስታን የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ቶማስ ዌስት እና በአሜሪካ ገንዘብ ሚኒስትር የሽብርንና የፋይናንስ ክትትል ምክትል ሚኒስትር ብሬይን ኔልሰን ከታሊባን ጋር ውይይት ያደረጉት የአሜሪካ ባለስልጣናት መሆናቸው ተገልጿል፡፡
አሜሪካ ቀደም ሲልም ከታሊባን መሪዎች ጋር በኳታር ዶሃ ውይይት አድርጋ እንደነበር ይታወሳል፡፡ የባለፈው ውይይትም በተመሳሳይ አሜሪካ ጥቅም ላይ እንዳይውል ባደረገችው አፍጋኒስታን ተቀማጭ ገንዘብ ዙሪያ የነበረ ሲሆን የዛሬውም ተመሳሳይ ጉዳይ መሆኑን የዋሸንግተን ባለስልጣናት አስታውቀዋል፡፡
አፍጋኒስታንን እያስተዳደረ ያለው ታሊባን ከአሜሪካ ጋር ተደጋጋሚ ውይይት እያደረገ ያለው አሜሪካ እንደማትለቅ ያሳወቀችውን ገንዘብ ለማስለቀቅ እንደሆነ እየተገለጸ ነው፡፡ በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር የአፍጋኒስታን ማዕከላዊ ባንክ ተቀማጭ ገንዘብ እስካን ለታሊባን አልተለቀቀለትም፡፡
ከቀናት በፊት የአሜሪካ ሹሞች እና የታሊባን ተወካዮች የአፍጋኒስታንን ተቀማጭ ገንዘብ ለመልቀቅ የሚያስችል ዕቅድ ማውጣታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ ምንም እንኳን የታሊባንና የአሜሪካ ሰዎች ንግግር ማድረጋቸው ቢገለጽም ልዩነቶች እንዳሏቸው ግን እየተሰማ ነው፡፡
አሜሪካ በአፍጋኒስታን ማዕከላዊ ባንክ ውስጥ ያሉ ከፍተኛ የፖለቲካ ሰዎች እንዲቀየሩ ብትፈልግም ታሊባን ግን ተቃውሟል ተብሏል፡፡ የማዕከላዊ ባንክ ከፍተኛ አመራር ከሆኑት መካከል አንደኛው በአሜሪካ ማዕቀብ የተጣለባቸው እንደሆኑም ዘገባው ጠቅሷል ፡፡