ድሮኑ የአየር እና የባህር መከላከያዎችን በማምለጥ ድንገተኛ ጥቃት መሰንዘር ይችላል
ቻይና በአይነቱ ለየት ያለ ባህር ስር እንደ ሰርጓጀ አየር ላይ ደግሞ ድሮን የሚሆን መሳሪያ እየሰራች መሆኑ ተሰምቷል።
የቻይና ተመራማሪዎች እየሰሩት ነው የተባለው አዲሱ ስተሊዝ ድሮን ታጣፊ ክንፍ የተገጠመለት ሲሆን፤ ከባህር ስር ወጥቶ ሲበር ክንፎቹ የሚዘረጉ ይሆናል።
የኒንጃንግ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች አሁን ላይ ለናሙና የሚሆን አዲሱን ሰርጓጅ እና አየር ላይ በራሪ ድሮን በመስራት ሙከራ እያደረጉበት መሆኑም ታውቋል።
ሳውዝ ቻይና ሞኒተሪንግ ፖስት ጋዜጣ ባወጣው መረጃ፤ ድሮኑ አራት ተሸከርካሪ ሞተሮች የተገጠሙለት ሲሆን፤ ሁለቱ ከፊት ሁለቱ ደግሞ ከኋላ የተገጠሙ ናቸው።
ደሮኑ በባህር ስር በሚሆንበት ጊዜ ሁለቱ ክንፎቹን በማጠፍ የሚቀዝፍ ሲሆን፤ ይህም በጣም ዘመናዊ የሆነ የሰርጓጅ መርከብ ቅርጽ እንዲላበስ የሚያደርገው ነው።
ከባህር በመውጣት አየር ላይ በሚንሳፈፍበት ወቅት ደግሞ ክንፎቹን የሚዘረጋ ሲሆን፤ በሰዓት እስከ 120 ኪሎ ሜትር ድረስ መብረር የሚችል መሆኑንም የኒንጃንግ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች አስታውቀዋል።
ድሮኑ በባህር ስር እንዲሁም በአየር ላይ ፈጣን እና የረጅም ርቀት ተልእኮዎችን በቀላሉ መከወን የሚችል መሆኑን ፕሮፌሰር አንግ ሂሶንግ ገልፀዋል።
አዲሱ ድሮን ከራዳር እይታ ውጪ እንዲሆን ታስቦ መሰራቱን የሚያነሱት የዘርፉ ባለሙያዎች፤ ትክክለኛ ጥቅሙ የአየር እና የባህር መከላከያዎችን በማምለጥ ድንገተኛ ጥቃት ለመሰንዘር መቻሉ እንደሆነም ተናግረዋል።
ድሮኑ መቼ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ የቻይና ጦር ይታጠቀዋል በሚል ላይ እንዲሁም ድሮኑ ምን አይነት መሳሪያዎችን መታጠቅ ይችላል በሚለው ላይ የወጣ መረጃ የለም።