የቻይና ጦር በታይዋን ዙሪያ ሲያካሂድ የነበረውን ወታደራዊ ተልዕኮ ማጠናቀቁን አስታወቀ
የአሜሪካ አፈ ጉባዔ የታይዋን ጉብኝትን ተከትሎ በአከባቢው የተፈጠረው ውጥረት እንደቀጠለ ነው
“ለውጊያ ሙሉ በሙሉ ዝግጁ ለመሆን” ያለመው ልምምድ እንደሚቀጥል የቻይና ጦር አስታውቋል
ቻይና በታይዋን ዙሪያ ስታካሂዳቸው የነበሩትን የተለያዩ ወታደራዊ ተልዕኮዎችን ማጠናቀቋን አስታወቀች።
የቻይና ጦር፤ "አሁን ያለው ሁኔታ በታይዋን የባህር ዙሪያ ያለውን ለውጥ በቅርበት መከታተል ይፈልጋል" ሲል አሳስቧል።
ጦሩ “ለውጊያ ሙሉ በሙሉ ዝግጁ ለመሆን” ወታደራዊ ልምምድ ማድረጉን እንደሚቀጥል መጠቆሙም ቻይና ደይሊ ግሎባል ታይምስ ዘግቧል።
የአሜሪካ ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ናንሲ ፔሎሲ በታይዋን ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ፤ በሩቅ ምስራቅ የነገሰው ውጥረት እንደቀጠለ ነው።
አፈ ጉባኤዋ ባሳለፍነው ሳምንት ታይዋንን የጎበኙ ሲሆን ድርጊቱ ቻይናን እንዳስቆጣ የዓለም ብዙሀን መገናኛዎች ዘግበዋል።
ይሄንን ተከትሎም ቻይና በታይዋን ባህር ዙሪያ ለቀናት የሚዘለቅ ወታደራዊ ልምምድ በማድረግ ላይ መሆኗን አሳውቃ ነበር።
ቻይና ባሳለፍነው ሳምንት ልምምድ ላይ ዶንግ ፋንግ የተሰኘው የቻይና የረጅም እና አጭር ርቀት ባልስቲክ ሚሳኤሎች ወደ ታይዋን ባህር ተኩሳ እንደነበርም ሚታወስ ነው።
በታይዋን ስድስት አቅጣጫዎች ምንም አይነት የባህር እና አየር ላይ ትራንስፖርት እንቅስቃሴ እንዳይኖር ቻይና አስቀድማ ማስጠንቀቋ ይታወሳል።
በቻይና ድርጊት ከፍተኛ ስጋት ውስጥ የገባቸው ታይዋን በበኩሏ ቻይና “ለወረራ እየተዘጋጀች” መሆኑን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በመናገር ላይ ናት፡፡
የታይዋን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆሴፍ ዉ ቻይና “ለወረራ ለመዘጋጀት” የሚያስችላት ወታደራዊ ልምምድ እያደረገች መሆኗን መግለጻቸው ኤኤፍፒ ማክሰኞ እለት ዘግቧል፡፡
ጆሴፍ ው የቻይናን የሶሞኑ ወታደራዊ እንቅስቀሴ በማስመልከት በታይፔ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ ቤጂንግ በእስያ-ፓሲፊክ አካባቢ ያለውን ሁኔታ ለመቀየር እየሰራች ነው ብለዋል።
የቤጂንግ የጦርነት ጨዋታ “የታይዋንን መብት የሚጻረር” እና በታይዋን ዙሪያ ያለውን ውሃ እና ሰፊውን የእስያ-ፓሲፊክ ቀጠናን ለመቆጣጠር የተደረገ ሙከራ ነው” ብለዋል ጆሴፍ ው።
ቤጂንግ የአሜሪካ የተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ናንሲ ፔሎሲ ታይዋንን የሚጎበኙ ከሆነ ጦሯ “ዝም ብሎ እንደማይቀመጥ” ስታስጠነቅቅ መቆየቷ የሚታወስ ነው፡፡
እናም በምስራቅ ታይዋን የባህር አከባቢ የተፈጠረው ውጥረት ወዳልተፈለገ የጦር መማዘዝ እንዳያመራ ተሰግቷል።