ቻይና የሊባኖስን ሉኣዊነት መጠበቅ "በጽኑ እንደምትደግፍ" ገለጸች
ቻይና ይህን ያለችው እስራኤል በሌባኖስ ግዛት ውስጥ በአስርት አመታት እጅግ ከባድ የተባለ የአየር ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ ነው
ቻይና እስራኤል እና ፍልስጤም እንደሀገር ተመስርታ ጎን ለጎን እንዲኖሩ የሚያስችለው 'ቱ ስቴት ሶሉሽን' ተግባራዊ ይሁን የሚል አቋም አላት
"ቻይና የሊባኖስን ሉኣዊነት መጠበቅ "በጽኑ እንደምትደግፍ ገለጸች።
የእስያዊቷ ኃያል ሀገር ቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ይ ቻይና ሊባኖስ ሉኣዊነቷን ለመጠበቅ የምታደርገውን እንቅስቃሴ እንደምትደግፍ እና የሉአላዊነት መጣስን በጽኑ እንደምታወግዝ ለሊባኖስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አብዳላ በሸ ሀቢብ ነግረዋቸዋል።
ቻይና ይህን ያለችው እስራኤል በሌባኖስ ግዛት ውስጥ በአስርት አመታት እጅግ ከባድ የተባለ የአየር ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ ነው።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ዋንግ እና ሀቢብ በኒው ዮርክ ተገናኝተው በመካከለኛው ምስራቅ ጉዳይ ሀሳብ ተለዋውጠዋል።
እስራኤል በሊባኖስ የሚገኙ የሄዝቦላ ይዞታዎችን መምታቷን በገለጸችበት የትናንቱ ጥቃት ቢያንስ 492 ሰዎች መገደላቸውን እና በ10ሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ለደህንነታቸው ፈርተው መሸሻቸውን የሊባኖስ ባለስልጣናት ተናግረዋል።
ዋንግ ሁኔታዎች ቢቀያየሩም ቻይና "ሊባኖስን ጨምሮ ከአረብ ወንድሞች እና ከፍትህ ጎን" መቆሟን ትቀጥላለች ብለዋል።
ዋንግ "በተለይ በቅርቡ በሊባኖስ የተከሰተውን የመገናኛ መሳሪያዎች ፍንዳታን ጨምሮ በቀጣናው ያለውን ሁኔታ ትኩረት ሰጥተን እየተከታተልነው ነው። በሊባኖስ የተፈጸመውን ንጹሃንን ያልለየ ጥቃት እናወግዛለን" ማለታቸውን መግለጫው ጠቅሷል።
ዋንግ እንዳሉት ቻይና በመካከለኛው ምስራቅ ሰላም እንዲሰፍን ስትሰራ ቆይታለች፤ አሁንም ከአረብ ሀገራት እና ከአለማቀፍ ማህበረሰብ ጋር መስራቷን ትቀጥልበታለች። ዋንግ አክለውም ግጭትን በግጭት መመለስ የመካከለኛው ምስራቅን ችግር እንደማይፈታው ይልቁንም የከፋ የሰብአዊ ቀውስጥ እንደሚያስከትል ተናግረዋል።
የአሁኑ ግጭት የጋዛው ጦርነት መስፋፋቱን የሚያሳይ መሆኑን የገለጹት ዋንግ አለምከቀፉ ማህበረሰብ ግልጽ አቋም መያዝ እንዳለበትና የቀጣናው ሀገራትም አንድነት መፍጠር አንዳለባቸው ጠቅሰዋል ዋንግ።
ቻይና ዘላቂ ተኩስ አቁም እንዲደረግ እና እስራኤል እና ፍልስጤም እንደሀገር ተመስርታ ጎን ለጎን እንዲኖሩ የሚያስችለው 'ቱ ስቴት ሶሉሽን' እንዲተገበር ወታደሮች ሙሉ በሙሉ መውጣት አለባቸው የሚል አቋም አላት ብለዋል ዋንግ።