ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ብሪታኒያ ከቻይና ጋር የነበራት ወርቃማ ዘመን አብቅቷል አሉ
ሱናክ ቻይና ሁሉንም የመንግስት ኃይሎች በመጠቀም ለዓለም አቀፍ ተጽእኖ በግልጽ እየተፎካከረች ብለዋል
ጠቅላይ ሚንስትሩ የቻይናን የኮቪድ እንቅስቃሴ ገደብ በተቃወሙ ዜጎች አያያዝ እና የቢቢሲ ጋዜጠኞች “እስራትና ድብደባን” ተችተዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ "ወርቃማ ዘመን” ተብሎ የሚጠራው የእንግሊዝና የቻይና ግንኙነት ማክተሙን ተናግረዋል።
የቻይና መንግስት በብሪታንያ ፍላጎትና ጥቅም ላይ ባደረሰው "ስርዓታዊ ፈተና" የሁለትዮሽ ግንኙነቱ መሻከሩን ገልጸዋል።
አዲሱ የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚንስትር ባደረጉት የመጀመሪያ ትልቅ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ንግግር የቻይናን የሰብዓዊ መብት አያያዝ በመተቸት በእስያ ታላላቅ ሀገራት ላይ አካሄድ "ማሻሻል" እንደሚፈልጉ ተናግረዋል ።
ሆኖም ዩናይትድ ኪንግደም በዓለም ጉዳዮች ላይ የቻይናን አስፈላጊነት በቀላሉ ችላ ማለት እንደማትችል ያመኑት ሱናክ፤ አካሄዳቸው "የረጅም ጊዜ እይታን" እንደሚከተል አሳውቀዋል።
"እውነቱን እንነጋገር። ንግድ ወደ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ተሃድሶ ይመራል ከሚለው ግትር ሀሳብ ጋር በመሆን ወርቃማው ዘመን አክትሞለታል” ብለዋል።
"ነገር ግን ቀለል ባለ የቀዝቃዛ ጦርነት ንግግሮች ላይ መተማመን የለብንም ያሉር ሪሺ ሱናክ፤ ቻይና በእሴቶቻችን እና በጥቅማችን ላይ የስርዓት ተግዳሮት እንደፈጠረች እንገነዘባለን በማለት ሁኔታውን ገልጸዋል።
ይህም ፈተና ወደ የላቀ አምባገነንነት ስትሸጋገር የበለጠ እየጠናከረ ይሄዳል ማለታቸውን ዘ ቴሌግራፍ ዘግቧል። ።
ሱናክ ቻይና በሀገሪቱ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን የኮቪድ የእንቅስቃሴ ገደብ በተቃወሙ ዜጎቿ አያያዝ እና የቢቢሲ ጋዜጠኞች እስራትና ድብደባን በመተቸት፤ መንግስት የሰዎችን ስጋት ከማዳመጥ ይልቅ “የበለጠ እርምጃ መውሰድን መርጧል” ብለዋል ።