“አሜሪካ በቻይና ፖሊሲዎቿ ላይ የሰራችውን ስህተት ማረቅ አለባት”-ቻይና
የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሜሪካ የፈጸመቻቸውን ስህተቶች ማረም እንዳለባት ገልጸዋል
የአሜሪካ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የቻይናው አቻቸው ጋር በሰሜናዊ ቻይና ቲያንጂን ከተማ መወያየታቸው ተሰምቷል
ዋሸንግተን፣በቤጅንግ ፖሊሲዎች እና ድርጊቶች ላይ የፈጸመችውን ስህተት እንድታስተካክል እና እንድታቃና የቻይና ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አሳሰበ፡፡
የአሜሪካ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዌንዲ ሸርማን ከቻይናው አቻቸው ዥ ፌንግ ጋር በሰሜናዊ ቻይና ቲያንጂን ከተማ ውይይት ማድረጋቸው ተሰምቷል፡፡
በውይይታቸውም የቻይናው ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዥ ፌንግ አሜሪካ በቻይና ላይ የፈጸመቻቸውን ስህተቶች ማረም እንዳለባት ገልጸዋል፡፡ ቤጅንግ ሊስተካከሉ ይገባል ያለቻቸው ስህተቶች፤ በቻይና ባለስልጣናት ላይ የተጣለው ማዕቀብ፤ በተማሪዎች ላይ የተጣለው የቪዛ ዕገዳ እና የቻይናን ኢንተርፕራይዞች ጭቆና መሆናቸውን ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡
ከዚህ ባለፈም ቤጅንግ አሜሪካ ለቻይና ያላት እይታ ትክክል እንዳልሆነ ገልጻ ይህንንም መቀየር እንዳለባት የቻይናው ባለስልጣን መናራቸውን ሺንዋ ዘግቧል፡፡ ሁለቱ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ባደረጉት ውይይት የሀገራቱ ግንኙነት ከባድ ፈተናዎች ገጥመውታል ተብሏል፡፡
አሜሪካ፤ ቻይናን በአዕምሮ ጠላት አድርጎ መሳል ዋነኛ ሀገራዊ ዓላማ አድርጋ እንደያዘችም ነው የተገለጸው፡፡ በቤጅንግ እና ዋሸንግተን ባለስልጣናት መካከል ያለው አንድ ጥሩ ነገር ለንግግር መቀመጣቸው እንጅ ግንኑነቱ መሻከሩ የሚካድ እንዳልሆነ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን እየዘገቡ ናቸው፡፡