የዓለም ጤና ድርጅት ባለሙያዎች የኮሮናቫይረስ መነሻን ለማጥናት ዉሃን እንደሚገቡ ቻይና አስታወቀች
2 ሚሊዮን ያክል ሰዎችን ለሞት የዳረገው የቫይረሱ መነሻ ጥናት ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል
የድርጅቱ ባለሙያዎች ቡድን ከቻይና ሳይንቲስቶች ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩ ቻይና ገልጻለች
ከዓመት በፊት በቻይና ዉሃን ተከስቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ መላውን ዓለም ያጥለቀለቀው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መነሻ ምክንያት ምን እንደሆነ በዓለም ጤና ድርጅት እንዲጠና ከተጠየቀ ቆይቷል፡፡
የቫይረሱን መነሻ ለማጥናት የዓለም ጤና ድርጅት ከቻይና መንግስት ጋር ሲነጋገር ቆይቶ ባለፈው ሳምንት ወደ ቻይና የላካቸው ባለሙያዎች ወደ ዉሃን እንዳያቀኑ የሀገሪቱ መንግሥት መከልከሉን የድርጅቱ ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሀኖም ገልጸው እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ ባለሙያዎቹ ያልሄዱት ባልተሟሉ የቪዛ ምክንያቶች መሆኑን የገለጸው የቻይና መንግሥት ፣ ከቀጣዩ ሀሙስ ጀምሮ 10 የዓለም ጤና ድርጅት ባለሙያዎች ቻይናን እንደሚጎበኙ አስታውቋል፡፡
የድርጅቱ ባለሙያዎች ቡድን ከቻይና ሳይንቲስቶች ጋር በቅንጅት የቫይረሱን መነሻ እንደሚመራመሩ የቻይና ብሔራዊ የጤና ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ ይፋ አድርጓል፡፡
ካለፈው ዓመት ጀምሮ ውይይት እየተደረገበት ለረዥም ዓመታት የተጠበቀው መነሻውን የማጣራት ጉዳይ ፣ ከፍተኛ የፖለቲካ ጉዳይም ሆኖ ቆይቷል፡፡ አሜሪካ እና አውስትራሊያ የቫይረሱ መነሻ ምክንያት እንዲጠና ሲወተውቱ የቆዩ ሲሆን አሜሪካ ከዓለም ጤና ድርጅት እስከመውጣትም ደርሳለች፡፡ 2 ሚሊዮን ያክል ሰዎችን ለሞት የዳረገው የኮሮናቫይረስ የዓለምን ኢኮኖሚም ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ የከተተ ጉዳይ ነው፡፡
የብዙ ቀውሶች ምክንያት የሆነውን የኮሮና (ኮቪድ-19) መነሻ ለማጥናት ወደ ቻይና የገቡ የዓለም ጤና ድርጅት ባለሙያዎች ፣ ስራቸውን ከመጀመራቸው በፊት ፣ ለ 2 ሳምንታት ራሳቸውን ለይተው እንደሚቆዩ ይጠበቃል፡፡
ቫይረሱ በተከሰተበት ጊዜ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ግንዛቤ እንዲኖረው አላደረገችም በሚል ቻይና ከፍተኛ ትችት አስተናግዳለች የፍራንስ 24 ዘገባ እንደሚያሳየው፡፡