በወቅቱ ሪፖርት የተደረገው 50 ሺ ያህል ሰዎች ብቻ በቫይረሱ ተይዘው እንደነበር ነው
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መነሻ ተደርጋ በምትጠቀሰው የቻይናዋ ውሃን ከተማ በቫይረሱ ተይዘው የነበሩ ሰዎች ቁጥር ሪፖርት ከተደረገው ምናልባትም በ10 እጥፍ ሊበልጥ እንደሚችል ተነገረ፡፡
የቻይና የበሽታዎች ቁጥጥር ማዕከል ባሳለፍነው ወርሃ ሚያዚያ 11 ሚሊዬን ከሚጠጋው የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል 4 ነጥብ 4 በመቶ ያህሉ ጸረ ኮሮና እንግዳ አካልን በሰውነታቸው አዳብረው እንደነበር አሳውቋል፡፡
ይህ በወቅቱ 480 ሺ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው እንደነበር የሚያመለክት ነው፡፡
ሆኖም በወቅቱ ሪፖርት የተደረገው 50 ሺ ያህል ሰዎች ብቻ በቫይረሱ ተይዘው እንደነበር ነው፡፡
ቻይና በቫይረሱ ተይዘው ነገር ግን ምልክቶቹን የማያሳዩ የቫይረሱ ተጠቂዎችን ቁጥርም አላካተተችም፡፡ ይህም በእውነተኛው የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ላይ ልዩነትን አምጥቷል እንደ ኤኤፍፒ ዘገባ፡፡
በቻይና 87 ሺ 27 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ የ4 ሺ 634 ሰዎች ህይወት ማለፉን የሃገሪቱ ብሄራዊ ጤና ኮሚሽን መረጃ አመልክቷል፡፡
የጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ በቫይረሱ የተያዙትን ቁጥር 96 ሺ 513 ያደርሰዋል፡፡
ቻይና ከማዕከላዊ ሃገሪቱ ክፍል ተነስቷል የሚባልለትን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የያዘችበት መንገድ ሲያስወቅሳት ነበረ፡፡ ምንነቱ ያልታወቀ አዲስ ቫይረስ መከሰቱን በማስታወቅ የአያያዙን ሁኔታ ሲያጋልጡ የነበሩ ሰዎችን ዝም ለማሰኘት ሞክራለች በሚልም ጠንከር ያሉ ወቀሳዎችን አስተናግዳለች፡፡