“ቀዝቃዛው ጦርነት እንዲደገም መፍቀድ የለብንም” የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር
ሁለቱ ሀገራት ከአስርት ዓመታት በኋላ ግንኙነታቸው ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል
ቻይና ከአሜሪካ ጋር ያላትን አለመግባባት በዉይይት የመፍታት ፍላጎት እንዳላት አስታወቀች
“ቀዝቃዛው ጦርነት እንዲደገም መፍቀድ የለብንም” የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር
የቻይናው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ከ50 ዓመት በፊት የነበረው ቀዝቃዛው ጦርነት ራሱን እንዲደግምና ዓለም እንዲጎዳ መፍቀድ እንደማይገባ አስታውቀዋል፡፡ ሚኒስትሩ ሀገራቸው ከአሜሪካ ጋር ባላት ታሪካው እና ወቅታዊ ግንኙነት፣ የቀዝቃዛው ጦርነት ድጋሚ ይጀመር ይሆን ወይ በሚለው ሃሳብ ፣ በሆንግ ኮንግና በሰሞነኛው የዋሸንግተን ባላሥልጣናት አስተያየት ዙሪያ ከሀገሪቱ ዜና አገልግሎት ሽንዋ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡
ዋንግ ዪ አሜሪካና ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ችግሮች እንደነበሩ ገልጸው ለዚህም የዋሽንግተን ፖለቲከኞችን ተጠያቂ አድርገዋል፡፡ የዚህ መነሻም የቤጂንግና የዋሸንግተንን ግንኙነትን ዝቅ ማድረግና ዋጋ የለውም ብሎ ማጠልሸት እንደሆነ ነው ያስታወቁት፡፡ አሁን ላይ ቀድሞ የነበረውን ቀዘቃዛውን ጦርነት ለመመለስና ዳግም እንዲከሰት ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት ማስቆም እንደሚገባም ነው የገለጹት፡፡
የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ ከቻይና ጋር ከአራት አስርት ዓመታት ጀምሮ የነበረው ግንኙነት ምንም ውጤት እንዳላመጣ ከሰሞኑ ሲገልጹ ነበር፡፡ ዋንግ ይ ግን የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ኒክሰን እ.ኤ.አ. በ1972 በቻይና ባደረጉት ጉብኝት ከቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር ዙአ ኢንላይ ጋር ባደረጉት ውይይት ሀገራቱ ከልዩነቶቻቸው ይልቅ መግባባት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ እንዲሰሩ ለማድረግ መስማማታቸውን አስታውሰዋል፡፡
የአሁኑ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ቻይና የበለጠ እየተጠቀመች ሲሆን አሜሪካ ደግሞ በአንጻሩ እየተጎዳች ነው በሚል በተደጋጋሚ እያነሱ ላለው ቅሬታ የቻይናው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ሁለቱም ሀገራት ግንኙነታቸው በማደጉ ጥቅሙ የጋራ ስለመሆኑ ያነሱት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የቤጂንግና የዋሽንግተን ግንኙነት በአሜሪካ ብቻ 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሥራዎች እንዲፈጠሩ አድርጓል ብለዋል፡፡ ዋንግ ዪ ከ70 ሺ በላይ የአሜሪካ ነጋዴዎች በቻይና እየሰሩ መሆናቸውንና 700 ቢሊዮን ዶላር የሚሆን ገንዘብ እያንቀሳቀሱ መሆናቸውን ገልጸው ከዚህ ውስጥ 97 በመቶ የሚሆኑት ትርፋማ እንደሆኑ አንስተዋል፡፡ “አሁን ላይ የኮሮና ተጽዕኖ ቢኖሮም አሜሪካውያን ነጋዴዎች ግን አሁንም በቻይና የመቆየትና የመስራት ፍላጎት አላቸው ይህ ደግሞ የሀገራቱን ግንኙነት ጠቀሜታ ያሳያል” ነው ያሉት፡፡
ይሁንና አሁን አሜሪካ የምታራምደውን አጀንዳ የተቹት ዋንግ ዪ “ይህ አካሔድ ዓለምን ወደ ክፍፍልና ወደ ሥርዓት አልበኝነት ያመራል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ቤጂንግ ይህንን ሁኔታ እንደማትፈቀድም የገለጹት ሚኒስትሩ ዓለምን ያከሰረው ቀዝቃዛው ጦርነት በድጋሚ እንዲከሰት መፍደቀድ ተጨማሪ ኪሳራ ነው ብለዋል፡፡
አሁን ላይ በ21ኛው ሁሉም ሀገራት ልማትና ሰላም ይፈልጋሉ ያሉት ዋግ ይ ከዚህ በተቃራኒ መሄድ ግን ከታሪክ በተቃራኒ መቆም እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የአሁኗ ቻይና የቀድሞሟ ሶቪየት ሕብረት አይደለችም የሚሉት የቻይናው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሌላኛዋ አሜሪካ የመሆን ፍላጎትም እንደሌላቸው ነው ያነሱት፡፡
ቻይና በቅርቡ ያወጣችውን የሆንግ ኮንግ የጸጥታ ሕግ በተመለከተ አሜሪካ ከፍተኛ ተቃውሞ ማንሳቷንና ጉዳዩን ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት እንደምትወስድ መግለጿ ቻይናን አስቆጥቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ዋንግ ዪ ቻይና የፖለቲካ ጽንስ ሃሳብን በሌሎች ሀገራት ላይ እንደማትጭንና በሌሎች ሀገራት ጉዳይ ጣልቃ እንደማትገባ በመግለጽ ለአሜሪካ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የአሜሪካ አስተዳደር በቅርብ ጊዜያት በቻይና ላይ እምነት እያጣ ስለመሆኑ ከሽንዋ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ “በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ግንኙነት ዋነኛው ሥራ መሆን ያለበት መነጋገር ብቻ ነው ፤ ቻይናም በዚህ ታምናለች” ብለዋል፡፡
በመጨረሻም “ቻይና ኃላፊነት የሚሰማት ሀገር ናት” ያሉት ዋንግ ዪ ከአሜሪካ ጋር አሁን ያለውን ችግርና አለመግባባት ለመፍታት ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል፡፡ ይህን ለማድረግም ሀገራቸው በማንኛውም ጊዜ በየትኛውም ደረጃ ለመነጋገር ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል፡፡
አሜሪካ በሆንግ ኮንግ ጉዳይ ጣልቃ መግባት እንደሌለባት በማሳሰብ “ጉዳዩ የውስጥ ጉዳይ ብቻ መሆኑን እናምናለን ፤ በሌላ ሀገር ጉዳይ ጣልቃ መግባት የማይፈቀድ ጉዳይ ነው” ብለዋል፡፡
አሜሪካ ብቻ ሳትሆን የአውሮፓ ሀገራትም የሆንግ ኮንግን የጸጥታ ሕግ መቃወማቸውን አውግዘዋል፡፡ ሩሲያ በአንጻሩ ጉዳዩ ውስጣዊ ነው በማለት ከቤጅንግ ጎን ቆማለች፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን በዋሽንግተንና ቤጂንግ መካከል እሰጥ አገባዎች ቀጥለዋል፡፡
ከቆየው የንግድ ጦርነታቸው ፣ በሆንግ ኮንግ እና ታይዋን ጉዳይ ያላቸው አለመግባባት ፣ የኮሮና ቫይረስ እና መሰል ጉዳዮች እንዳሉ ሆነው በቅርቡ ሁለቱም ሀገራት አንድ አንድ ቆንስላ ጽ/ቤት መዝጋታቸው እንዲሁም ትራምፕ የቻይናውን የአጭር ቪዲዮዎች ማጋሪያ ቲክቶክን በአሜሪካ አገልግሎት እንዳይሰጥ ለመከልከል በቅርቡ መዛታቸው የሀገራቱን ግንኙነት እየሻከረ መሔዱን አመላካች ነው፡፡ በአጠቃላይ የሁለቱ ሀገራት ግኝኙነት ከ5 አስርት ዓመታት በኋላ ዝቅተኛ የሚባል ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡