ቻይና ትዳር የመሰረቱ ዜጎቿን እንደምትሸልም ገለጸች
አዲስ ተጋቢ ቻይናዊያንን ለማበረታታት የ97 ሺህ ዶላር ሎተሪ እና ስጦታዎች ተዘጋጅቷል ተብሏል
በቻይና አዲስ የሚወለዱ ህጻናት ቁጥር በየዓመቱ እያሽቆለቆለ እንደሚገኝ ተገልጿል
ቻይና ትዳር የመሰረቱ ዜጎቿን እንደምትሸልም ገለጸች፡፡
ከሕንድ ቀጥሎ ሁለተኛዋ ባለ ግዙፍ ህዝብ ቁጥር ባለቤት የሆነችው ቻይና በየዓመቱ የሚወለዱ ህጻናት ቁጥር እየቀነሰባት ይገኛል፡፡
ሀገሪቱ በየዓመቱ የሚወለዱ ህጻናትን ቁጥር ለመጨመር የተለያዩ ማበረታቻዎችን በማድረግ ላይ ስትሆን አሁን ደግሞ ዢያን የተሰኘችው ግዛት አዲስ ትዳር ለሚመሰርቱ የግዛቲቱ ነዋሪዎች ሽልማት አዘጋጅታለች፡፡
እንደ ሮይተርስ ዘገባ ይህች ግዛት አዲስ ተጋቢዎች የጋብቻ ማስረጃቸውን ለሚያቀርቡ ዜጎች የሎተሪ እጣ ያዘጋጀት ሲሆን አሸናፊዎች የ97 ሺህ ዶላር ሽልማት እና ሌሎች ስጦታዎችን እንደምትሰጥ አስታውቃለች፡፡
ጦርነቱን ተከትሎ በመደፈሯ ልትመሰርት የነበረው ትዳር የቀረባት ወጣት አሳዛኝ ታሪክ
በዢያን ግዛት ያሉ ተጋቢዎችን ከመጋቢት አንድ ጀምሮ እስከ ቀጣዩ ህዳር ወር ድረስ የሚያገቡ ጥንዶችን የተለያዩ ማበረታቻዎችን እንደሚሰጥ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
ቻይና ላለፉት ዓመታት ዜጎቿ ከአንድ ልጅ በላይ እንዳይኖራቸው የሚከለክል ህግ የነበራት ሲሆን ይህን ፖሊሲ ወደ ሁለት ልጅ ብታሻሽልም ዜጓቿ ልጅ የመውለድ ፍላጎታቸው እየቀነሰ መጥቷል ተብሏል፡፡
በቻይና የተጋቢዎች ቁጥር መቀነስ፣ ልጅ ወልዶ ለማሳደግ የሚፈጀው ገንዘብ ከፍተኛ መሆን እና ከትዳር ውጪ ለሚወለዱ ህጻናት መንግስታዊ አገልግሎቶችን መከልከል አዲስ ለሚወለዱ ህጻናት ቁጥር መቀነስ ዋነኛ ምክንያቶች እንደሆኑ ተገልጿል፡፡
በእስያ በተለይም በጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያ እና ቻይና አዲስ የሚወለዱ ህጻናት ቁጥር በየዓመቱ እየቀነሰ ሲሆን መንግስታት ዜጎቻቸው ልጆችን እንዲወልዱ በማበረታታት ላይ ናቸው፡፡