ቻይና ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የገንዘብ ኖቶችን በሙቀት ማጽዳት እና ማቃጠል ጀመረች
ቻይና ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የገንዘብ ኖቶችን በሙቀት ማጽዳት እና ማቃጠል ጀመረች፡፡
የቻይና ማዕከላዊ ባንክ ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል አዲስ ስትራቴጂ መተግበር ጀምሯል፡፡ ይሄም ቫይረሱ በተሰራጨባቸው አካባቢዎች የሚዘዋወሩ የገንዘብ ኖቶችን በከፍተኛ ሙቀት ከቫይረሱ ማጽዳት እና እስከ 14 ቀን ማቆየት ከዚያም ሲያልፍ በንክኪ ብዛት ቫይረሱ ሊኖርባቸው እንደሚችል በከፍተኛ ደረጃ የሚገመቱ ኖቶችን ማቃጠል ነው፡፡
ይህ የሚሆነው ቫይረሱ ለረዥም ሰዓታት ሳይሞት እንደሚቆይ በዓለም ጤና ድርጅት በመረጋገጡ ነው፡፡
የሚቃጠሉት ኖቶች ከሆስፒታል እና ከፍተኛ ተጠቂዎች ከሚኖሩባቸው አካባቢዎች ተሰብስበው፣ አስፈላጊው ህክምና ከተደረገላቸው በኋላ ወደ ማዕከላዊው ባንክ የሚላኩት ናቸው፡፡ ማዕከላዊ ባንኩ አስጊ እንደሆኑ ያመነባቸውን እነዚህን የገንዘብ ኖቶች መልሶ ወደ ገበያ ከማስገባት ይልቅ እንደሚያቃጥላቸው ነው ሲኤንኤን የዘገበው፡፡
በሚቃጠሉት ኖቶች ምትክም ባንኩ አዲስ የገንዘብ ኖቶችን አትሞ እንደሚያሰራጭ አስታውቋል፡፡
የገንዘብ ኖቶች የተለያዩ በሽታዎችን ከሰው ወደ ሰው የማስተላለፍ እድል እንዳላቸው በአውሮፓውያኑ 2017 በአሜሪካ የተደረገ ጥናት ያመለክታል፡፡ በዚሁ ዓመት በዶላር ላይ በተደረገ ጥናት ገንዘቡ የተለያዩ ተላላፊ ባክቴሪያዎች እና ቫይረሶች እንደሚገኙበት ተረጋግጧል፡፡
ይሁን እንጂ በገንዘብ በሽታዎች የመተላለፍ አቅማቸው እጅግ አናሳ ነው፡፡ ያም ሆኖ የኮሮና ቫይረስ አስጊነቱ ከፍተኛ በመሆኑ ነው ቻይና እርምጃውን መውሰድ የጀመረችው፡፡
እስካሁን በቫይረሱ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር 1,775 ሲደርስ (3 ከቻይና ውጭ)፣ 10,844 ሰዎች በቻይና ከቫይረሱ አገግመዋል፡፡ የተጠቂዎች ቁጥር ደግሞ በትናንትናው እለት በቻይና በ2,048 ጨምሮ (ከነዚህም 1,933ቱ ከሁቤይ ግዛትብቻ ናቸው) 70,635 ደርሷል፡፡ ከቻይና ውጭ ደግሞ 688 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ ሆነዋል፡፡
የዳያመንድ ፕሪንሰስ ክሩይዝ መርከብ ትናንት ተጨማሪ 99 ተጠቂዎች የተገኙበት ሲሆን በመርከቡ ውስጥ ከሚገኙ 3,700 ሰዎች እስካሁን የተጠቁት 454 ደርሰዋል፡፡ በመርከቡ ዉስጥ በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጠ ሰዎች መካከል ከ60 በላይ አሜሪካውያን ይገኛሉ፡፡
መርከቧ ሙሉ ተሳፋሪዎችን እንደያዘች በጃፓን ወደብ ለ14 ቀናት በማቆያነት እንድትቆይ ከተደረገች በኋላ አሜሪካ በዛሬው እለት 300 ዜጎቿን ከመርከቡ አስወጥታ ወደ ሀገሯ መልሳለች፡፡ ሌሎች ሀገራትም መሰል እርምጃ ለመውሰድ እየተሰናዱ ነው፡፡
ቻይና ቫይረሱን ለመቆጣጠር በምታደርገው ጥረት 780 ሚሊዮን ያክል የሚሆና ግማሹ ህዝቧ በተለያየ መጠን የጉዞ እገዳ ውስጥ ይገኛል፡፡
ምንጭ፡- ሲኤንኤን