የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር ባለፉት 3 ተከታታይ ቀናት እየቀነሰ መጥቷል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር ባለፉት 3 ተከታታይ ቀናት እየቀነሰ መጥቷል፡፡
ባለፉት ሶስት ቀናት በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱን የቻይና ባለስልጣናት አስታውቀዋል፡፡
በሀገሪቱ ትናንት 2,009 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተገለጸ ሲሆን 142 ሰዎች ሞተዋል፡፡ ባጠቃላይ እስካሁን በቻይና 1,666 ከቻይና ውጭ በፊሊፒንስ፣ ጃፓን እና ፈረንሳይ የ3 ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡ 68,584 በቻይና 510 ከቻይና ውጭ በድምሩ 69,094 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ተይዘዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት የተጠቂዎች ቁጥር በአያሌው እየጨመረ መሄድ ከፍተኛ ስጋትን ፈጥሮ የነበረ ቢሆንም፣ ቫይረሱ እንዳይሰራጭ የሚወሰዱ እርምጃዎች እየተጠናከሩ በመምጣታቸው ካለፈው አርብ እለት ጀምሮ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ሪፖርት እየቀነሰ መጥቷል፡፡
በሀገረ ቻይና ደግሞ የቫይረሱ መነሻ ከሆነው የሁቤይ ግዛት ውጭ ላለፉት 12 ቀናት የተጠቂዎች ቁጥር እየወረደ እንደመጣ ነው የቻይና ጤና ኮሚሽን ያስታወቀው፡፡ በትናንትናው እለት በ30 የሀገሪቱ ግዛቶች 166 ተጠቂዎች ብቻ እንደተገኙ ተዘግቧል፡፡ ይሄም ከ13 ቀናት በፊት እኤአ የካቲት 3 ከነበረው የ890 ሰዎች በቫይረሱ የመያዝ ሪፖርት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ መቀነስ መኖሩን የሚያሳይ ነው፡፡
የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ እንዳሉት የተጠቂዎች ቁጥር መቀነስ ቫይረሱን መቆጣጠር እንደሚቻል ማሳያ ነው፡፡
ከቻይና ውጭ 30 የሚሆኑ ሀገራት ቫይረሱ የተዛመተባቸው ሲሆን በነዚህ ሀገራት እስካሁን ከተመዘገበው 510 የተጠቂዎች ቁጥር መካከል አብዛኛውን ድርሻ የሚወስደው በጃፓን ወደብ የቆመው የዳያመንድ ፕሪንሰስ ክሩይዝ መርከብ ነው፡፡
ያሳፈራቸውን 3700 ሰዎች እንደጫነ በማቆያነት እንዲቆይ በተደረገው በዚህ መርከብ ውስጥ ትናንት የተለዩትን 70 ሰዎች ጨምሮ 355 ሰዎች በቫይረሱ ተጠቅተዋል፡፡ ከነዚህም 46 ሰዎች አሜሪካውያን ናቸው፡፡ ሀገሪቱ ይሄን ተከትሎ በመርከቡ ውስጥ የሚገኙ ዜጎቿን ወደ ሀገራቸው በመመለስ ለ14 ቀናት በለይቶ ማቆያ ስፍራ ክትትል ልታደርግላቸው ወስናለች፡፡
በሽታው ከተያዘው ዓመት ሊሻገር እንደሚችል የተገመተ ሲሆን ይሄም በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ተተንብዯል፡፡
በቻይና በአሁኑ ወቅት በርካታ ቢዝነሶች የተዘጉ ሲሆን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎቿ ስራቸውን በቤታቸው ሆነው ነው በማከናወን ላይ የሚገኙት፡፡
የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ኢኮኖሚያቸውን ከከፋ ጉዳት ለመታደግ የቢዝነስ ተቋማት ቶሎ ወደቀድሞ ስራቸው ሊመለሱ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ዢ በቤጂንግ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ማእከልን ሲጎነኙ
የችግሩ ሰለባ ደግሞ ቻይና ብቻ አይደለችም፡፡ የተቀረውም ዓለም ከቻይና የቢዝነስ ተቋማት መዘጋት ጋር በተያያዘ የአቅርቦት ችግር እየገጠመው ነው፡፡
ይሁንና አሁን ያለውን የኢኮኖሚ ሁኔታ መቆጣጠር ይቻላል የሚሉት የኢኮኖሚ ባለሙያዎች፣ የቫይረሱን ስርጭት ቶሎ መግታት ካልተቻለ ግን ነገሮች አሳሳቢ ይሆናሉ ብለዋል ከተለያዩ ምንጮች ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው፡፡