በቻይና ከ1 ሺ 700 በላይ የጤና ባለሙያዎች በኮሮና ቫይረስ ተያዙ
በቻይና ከ1 ሺ 700 በላይ የጤና ባለሙያዎች በኮሮና ቫይረስ ተያዙ፡፡
የኮሮና ቫይረስ እስካሁን ከ1,380 በላይ ሰዎችን በሞት ሸኝቷል፡፡ ከትናንት ወዲያ 242 ሰዎች በአንድ ቀን መሞታቸው በክብረወሰን የተመዘገበ ሲሆን በትናንትናው እለት ቁጥሩ በግማሽ ቀንሶ የ121 ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡
ባጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ደግሞ ከ64,400 በላይ ደርሷል፡፡ በቫይረሱ ከተያዙት 505ቱ ከቻይና ውጭ ባሉ 24 ሀገራት የሚኖሩ ሰዎች ናቸው፡፡ ከ6,000 በላይ ሰዎች ደግሞ ከቫይረሱ አገግመው ከሆስፒታል ወጥተዋል፡፡
በቻይና የቫይረሱን ተጠቂዎች በማከም ላይ የነበሩ 1,716 ሀኪሞች በቫይረሱ ከተያዙት መካከል መሆናቸው ተገልጿል፡፡ ከነዚህም ቫይረሱን በተመለከተ የመጀመሪያ መረጃ ያወጣውን ዶ/ር ሊ ዌንሊያንግን ጨምሮ ስድስቱ መሞታቸውን የቻይና ጤና ኮሚሽን ይፋ አድርጓል፡፡
90 በመቶ የሚሆኑት ተጎጂዎች ደግሞ የቫይረሱ መነሻ የሁቤይ ግዛት ሀኪሞች ናቸው፡፡ ከሁቤይ ግዛትም የግዛቲቱ ዋና ከተማ ዉሀን ብቻ 1,102 ሀኪሞች በቫይረሱ የተጠቁባት ሲሆን ይሄም 73 በመቶው ተጠቂዎች በከተማዋ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች መሆናቸውን ያሳያል፡፡
ይህ የሀኪሞች ለቫይረሱ በከፍተኛ ደረጃ መጋለጥ ለሀገሪቱ ሌላ ጭንቀት ሆኖባታል ነው የተባለው፡፡ የህክምና ቁሳቁሶች እጥረት ደግሞ ለችግሩ መፈጠር በዋና ምክኒያትነት ተጠቅሷል፡፡
የቻይና ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ በቤጂንግ አንድ ሆስፒታል ሀኪሞችን እየጎበኙ
11 ሚሊዮን ህዝብ የሚኖርባት ዉሀን 398 ሆስፒታሎች እና 6,000 ገደማ ክሊኒኮች አሏት፡፡ ይሁንና የሀገሪቱ ጤና ኮሚሽን ለኮሮና ቫይረስ ህክምና ተጨማሪ 9 ሆስፒታሎችን አስገንብቷል፡፡ 61 ሆስፒታሎች ደግሞ ታማሚዎችን ለማስተናገድ ተጨማሪ ዝግጅት አድርገዋል፡፡
የቫይረሱ ስርጭት በቻይና በተለይም በሀገሪቱ ሁቤይ ግዛት አሁንም አሳሳቢ ደረጃ ላይ መሆኑን ያስታወቀው የዓለም ጤና ድርጅት፣ ከቻይና ውጭ ያለው ስርጭት ግን የሚያሰጋ እንዳልሆነ ይፋ አድርጓል፡፡
ከቻይና ውጭ ባለው ስርጭት አሳሳቢ ሊባል የሚችለው ጃፓን ላይ 3,700 ሰዎችን እንዳሳፈረች የቆመችው ዳያመንድ ፕሪንሰስ ክሩይዝ መርከብ ጉዳይ ነው፡፡ መርከቧ ላይ ትናንት 44 ተጨማሪ ተጠቂዎች የተገኙ ሲሆን አጠቃላይ የተጠቂዎች ቁጥር 218 ደርሷል፡፡
ትናንት የካቲት 05 ቀን 2012 ዓ.ም በቻይና-ጀርመን ስትራቴጂያዊ ውይይት ላይ ለመሳተፍ በጀርመን ጉብኝት ያደረጉት የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ቫይረሱ ድንበር የለሽ በመሆኑ ስርጭቱን ለመቆጣጠር መላው ዓለም መተባበር አለበት ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
እስካሁን ቻይና ባደረገችው ከፍተኛ ጥረት ቫይረሱ በሌሎች ሀገራት እንዳይስፋፋ ሆኗል ሲሉም ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
ለዘገባው የተለያዩ ምንጮችን በዋቢነት ተጠቅመናል፡፡