አዝለው ያሳደጉትን እናቱን አዝሎ መላ ቻይናን እያስጎበኘ ያለው ወጣት
በመኪና አደጋ መንቀሳቀስ ያቃታቸው እናቱን በጀርባው አዝሎ ለጉብኝት የወጣው ቻይናዊ መነጋገሪያ ሆኗል
ወጣቱ የእናቱን የምንጊዜም ምኞት ለማሳካት ሙሉ ንብረቱን ሽጧል
የ31 አመቱ ቻይናዊ ወጣት መንቀሳቀስ የማይችሉ (ፓራላይዝድ) እናቱን ለአመታት በጀርባው አዝሎ መላው ቻይናን ለማስጎብኝት እያደረገው ያለው ጥረት በአርዓያነት አስመስግኖታል፡፡
ሀገራቸውን ተዘዋውረው ለመጎብኝት ጽኑ ፍላጎት ያላቸው እናቱ በህይወት ወጣ ውረድ እና ልጆቻቸውን ለማሳደግ ያለባቸውን ሃላፊነት እየተወጡ ባሉበት የደረሰባቸው አስከፊ የመኪና አደጋ በአልጋ ላይ እንዲውሉ አስገድዷቸዋል፡፡
ዣው ማ የተባለው ወጣት እናቱን ፓራላይዝድ ያደረገውና አባቱን ደግሞ ህይወቱን ያሳጣው አደጋ ሲከሰት ገና የ8 አመት ታዳጊ ነበር፡፡
ከዚህ ጊዜ በኋላ እርሱ እና ታላቅ እህቱ እናታቸውን እና ራሳቸውን የመንከባከብ እንዲሁም የማስተዳደር ሃላፊነቱን ይዘው ዘለቁ፡፡
ወጣቱ ዣው ማ በጥጥ ለቀማ እና በተለያዩ የጉልበት ስራ ዘርፎች በመሰማራት የሚያገኘውን ገንዘብ እናቱን ለማሳከም አልፎም በዚንጂያንግ የራሱን ምግብ ቤት ለመክፈት አውሎታል፡፡
በደረሰባቸው ከፍተኛ ጉዳት መናገር የማይችሉት እንዲሁም ከወገባቸው በታች መንቀሳቀስ የማይችሉት እናቱ ቀስበቀስ የጤና ሁኔታቸው እየተሸሻለ ተስፋን እያገኙ ባሉበት አንድ ያልጠበቁት ነገር ከሚከታተሏቸው ሀኪሞች ተነገራቸው፡፡
ከጥቂት አመታት በፊት እናቱን የሚከታተሉት ዶክተሮች የመኪና አደጋው በአዕምሮ እና በአከርካሪያቸው ላይ የፈጠረው ጉዳት ሙሉ ለሙሉ መንቀሳቀስ እንዳይችሉ ሊያደርጋቸው እንደሚችል ነገሩት፡፡
በዚህ ጊዜ ነበር ዣው ማ የምንግዜም የወላጅ እናቱ ህልም የሆነውን ቻይናን ተዘዋውሮ የመጎብኝት ፍላጎት ለማሳካት ከጊዜ ጋር መሽቀዳደም የጀመረው፡፡
በውሳኔውም ቤት ፣ መኪና ፣ ሬስቶራንት እና በእጁ ላይ የሚገኙ ንብረቶቹን ሽጦ እናቱን በጀርባው አዝሎ ለጉብኝት ከቀየው ወጣ፡፡
በደረሰባቸው አደጋ ሙሉ ለሙሉ የአዕምሮ ጤናቸው ሳይታወክ እንዲሁም ሁኔታዎችን መገንዘብ እና የማድነቅ አቅማቸው ሳይደከም ጉብኝቱን ለማድረግ መወሰኑን የሚናገረው ወጣቱ በተቻለ መጠን ብዙ ጊዜ ከእናቱ ጋር ማሳለፍ እንደሚፈልግ ገልጿል፡፡
እስካሁን ባለውም የቲያንሻን ተራራን፣ የቲያንቺ ሀይቅን እና ሌሎች በዢንጂያንግ የሚገኙ ቦታዎችን እንዲሁም የቤጂንግ ቲያንመን አደባባይ እና ታላቁ የቻይና ግንብን ጎብኝተዋል።
አዛውንቷ እናት መናገር እና ስሜታቸውን መግለጽ ባይችሉም ሁሌም ለጉብኝት በሄዱባቸው ስፍራዎች እና በሚመለከቷቸው ነገሮች ደስተኛ መሆናቸውን በፈገግታ ይገልጻሉ፡፡
እናት እና ልጁ አመታትን የፈጀውን ጉዟቸውን የሚያሳዩ አጫጭር ተንቀሳቃሽ ምስሎች እና ፎቶዎችን “ዶዩን” በተባለው የቻይና ቲክቶክ ላይ ማጋራት ከጀመሩ በኋላ በሚሊየን የሚቆጠሩ ተከታዮችን ያፈሩ ሲሆን፤ አንዳንድ ተከታዮቻቸው የገንዘብ ድጋፍ ባያደርጉላቸው ኖሮ ጉብኝታቸውን እስካሁን መቀጠል ሊቸገሩ እንደሚችሉ ተነግሯል፡፡
ወጣቱ ዣው ወደ ቤቱ መች እንደሚለስ ሲጠየቅ “እናቴ እኔን አዝላ አሳድጋለች አሁን ደግሞ የኔ ተራ ነው፤ እናቴ ያለችበት የትኛውም ቦታ ቤቴ ነው፤ ይህን ጉዞ እያደረኩ ያለሁት እናቴ ከመሞቷ በፊት የሚስደስታትን ነገር አድርጌ ከጸጸት ራሴን ለማዳን ነው” ሲል መልሷል፡፡