የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአዲስ አበባ - ሻንጋይ በረራው ታገደ
ሆስፒታሉ በምርመራ ወቅትም ሆነ የውጤት ማስረጃ በመስጠት ሂደት የፈጸመው ስህተት እንደሌለ ለአል ዐይን ገልጿል
ከሲልክ ሮድ ሆስፒታል የኮሮና ውጤት ይዘው በበረሩ አንዳንድ መንገደኞች ላይ ቫይረሱ መገኘቱ ለዕገዳው ምክንያት ነው ተብሏል
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአዲስ አበባ - ሻንጋይ በረራው ታገደ
ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ የአዲስ አበባ - ሻንጋይ በረራው መታገዱን የሚገልጽ ማስታወቂያ ከቻይና ባለሥልጣናት እንደደረሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ገልጿል፡፡ የበረራ እገዳው ምክንያት ከአዲስ አበባ ሻንጋይ ከተጓዙ መንገደኞች መካከል በአውሮፕላን ማረፊያዎች መድረሻ በሚከናወኑ የፒ.ሲ.አር. (PCR) ምርመራዎች አንዳንድ ተሳፋሪዎች የኮሮናቫይረስ አዎንታዊ ምርመራ ከተደረገ በኋላ ነው ፡፡
ምንም እንኳን መስፈርቶችን በጥብቅ ተግባራዊ በማድረግ አየር መንገዱ የኮሮናቫይረስ ምርመራ አድርገው ቫይረሱ እንደሌለባቸው የሚገልጽ ማስረጃ ያላቸውን ተሳፋሪዎች ብቻ አሳፍሮ የሚጓዝ ቢሆንም ጥቂት ተሳፋሪዎች በመድረሻ ላይ በተደረገላቸው ምርመራ ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ነው አየር መንገዱ ያስታወቀው፡፡
ቫይረሱ የተገኘባቸው ተሳፋሪዎች በአዲስ አበባ ከሚገኘው የቻይናው ሲልክ ሮድ አጠቃላይ ሆስፒታል የኮቪድ-19 ማዕከል ፣ ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸውን የሚያሳይ የፒ.ሲ.አር. ውጤት ማስረጃ ይዘው በአየር መንገዱ የበረሩ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራውን ለማስቀጠል ከቻይና ባለስልጣናት ጋር በጉዳዩ ላዙሪያ እየተወያየ እንደሚገኝም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
“እንደተለመደው የደንበኞች ደህንነት ቀዳሚ ትኩረቴ ነው” ያለው የኢትዮጵያ አየር መንገድበመሆኑም ሁሉንም ዓለም አቀፍና ሀገራዊ ደንቦችን ማክበሩን እና ከሁሉም የጤና ባለሥልጣናት ጋር በመተባበር እንደሚቀጥል ነው የገለጸው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከሲልክ ሮድ ሆስፒታል የሚመጡ የፒ.ሲ.አር. የምርመራ ውጤቶችን ከዚህ በኋላ መቀበል እንዳቋረጠ የገለጸው አየር መንገዱ ተሳፋሪዎቹ በተጠቀሰው ሆስፒታል የኮሮና ቫይረስ ምርመራ እንዳያደርጉ አሳስቧል፡፡
ሆስፒታሉ ለአል ዐይን አማርኛ በስልክ እንደገለጸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሳምንት በፊት ረቡዕ ዕለት ለሆስፒታሉ በጻፈው ደብዳቤ የራሱ የምርመራ ማዕከል እንዳለው በመግለጽ ከዚህ በኋላ ለአየር መንገዱ ደንበኞች ምርመራ በሆስፒታሉ እንዳይደረግ አስታውቋል፡፡ ከዚህ ዉጭ በሆስፒታሉ ምርመራ ያደረጉ መንገደኞች ቫይረሱ ስለተገኘባቸው ነው የሚል ምክንያት አየር መንገዱ አልገለጸም ነው ያለው ሆስፒታሉ፡፡
ሲልክ ሮድ ሆስፒታል በኮሮናቫይረስ የምርመራ ማዕከሉ ከሌሎች የህክምና ማዕከላት የምርመራ ማዕከሎች በተለየ መልኩ ከምርመራ እስከ ውጤት ማስረጃ ድረስ በራሱ እንደሚሰጥ በመግለጽ ስራውን በአግባቡ ሲያከናውን እንደቆየ ለአል ዐይን አስታውቋል፡፡ ይሁንና ሆስፒታሉ ዋነኛ የኮሮና ውጤት ምርመራ ማዕከል እንደመሆኑ ምርመራ ያደረገላቸው ግለሰቦች ከውጤቱ በኋላ በተለያየ መልኩ ለቫይረሱ ተጋላጭ ሆነው በመድረሻ በተደረገላቸው ምርመራ ቫይረሱ ተገኝቶባቸው ሊሆን ይችላል ነው ያለው ሆስፒታሉ፡፡ አብዛኛውን የኮሮና ምርመራ ሲያደርግ እና የውጤት ማስረጃ ሲሰጥ እንደነበር የገለጸው ሆስፒታሉ ለአየር መንገዱ ደንበኞች የሚያደርገውን የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ደብዳቤው ከደረሰው ካለፈው ረቡዕ ጥቅምት 4/2013 ዓ.ም. ወዲህ ማቋረጡን ነው የገለጸው፡፡
አዲስ አበባ ሲልክ ሮድ አጠቃላይ ሆስፒታል እ.ኤ.አ. በ2017 የተገነባ የቻይና ሆስፒታል ሲሆን ቻይና እና ከኢትዮጵያ እንዲሁም ከአፍሪካ ጋር ያላትን ወዳጅነት ለማጠናከር በማሰብ የ ‘ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሺየቲቭ’ አካል ሆኖ የተገነባ ነው፡፡