የኢትዮጵያ አየር መንገድና የኤሚሬትሱ ሳናድ ኤሮቴክ የትብብር ስምምነት ተፈራረሙ፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድና በአውሮፕላን ኤንጂን ጥገና የሚታወቀው የተባበሩት አረብ ኤሚሬትሱ ሳናድ ኤሮቴክ ዛሬ የትብብር ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
ስምምነቱን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገ/ማሪያም እና የሳናድ አቻቸው ማንሱር ጃናሂ ናቸው የተፈራረሙት፡፡
ሁለቱ አካላት የተፈራረሙት የ15 ዓመታት ስምምነት መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ስምምነቱም የሁለቱን ኩባኒያዎች አቅም በማስተባበር ብቁ የሰለጠነ የሰው ኃይል በመፍጠር የጋራ ቢዝነሳቸውን ለማሳደግ እንደሚረዳ አቶ ተወልደ ከፊርማው በኋላ ተናግረዋል፡፡
130 አውሮፕላኖች ያሉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በጥገናው ዘርፍ ትልቅ አቅም ካለው ሳናድ ጋር በትብብር መስራቱ ለእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ነው አቶ ተወልደ የተናገሩት፡፡
ለስምምነቱ መደረስ ከሁለቱም አካላት የተውጣጡ ተወካዮች ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውን በመጠቆም ለዚህም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
አቶ ተወልደ ገ/ማሪያም
የኤሚሬትሱ ሙባዳላ ኢንቨስትመንት ኩባንያ አካል የሆነው የሳናድ ዋና ስራ አስፈጻሚ ማንሱር ጃናሂ ባደረጉት ንግግር ደግሞ ኩባንያው ከተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ ውጭ በጋራ ለመስራት ስምምነት ሲፈጽም ይህ የመጀመሪያው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኩባንያው የመጀመሪያ ግንኙነቱን ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ያደረገው አየር መንገዱ ግዙፍና ገናና በመሆኑ ወደ አፍሪካ ገበያ ለመግባት በር ከፋች እንደሚሆን በማመን ነው ብለዋል፡፡
የሁለቱ ኩባንያዎች ትብብር እያደገ የመጣውን የሀገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማሳደግ እንደሚረዳም ተናግረዋል፡፡
ማንሱር ጃናሂ-መሀል ላይ ያሉት
ሁለቱ ኩባንያዎች ስምምነቱን የፈጸሙት አፍሪካን ትኩረቱ አድርጎ በአውሮፕላን ጥገና ዙሪያ ከተለያዩ የዓለማችን አየር መንገዶች የተውጣጡ ተሳታፊዎች የታደሙበት ስብሰባ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለበት ወቅት ነው፡፡
በአውሮፕላን ጥገና እና የአቪዬሽን አካዳሚ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ረዥም ልምድና አቅም ያለው መሆኑ ስብሰባው በአዲስ አበባ ለመካሄዱ ምክኒያት መሆኑን አቶ ተወልደ ገ/ማሪያም ገልጸዋል፡፡
በጥገና ዘርፍም አየር መንገዱ በአሁኑ ወቅት ለበርካታ የአፍሪካ አየር መንገዶች አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል ያሉት አቶ ተወልደ፣ ልምዱን በማካፈልም የእውቀት ሽግግር እያደረገ ነው ብለዋል፡፡ በአቪዬሽን አካዳሚውም አሁን ላይ 1,500 ሰልጣኞችን እያሰለጠነ የሚገኝ ሲሆን የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ሰልጣኞችም በአካዳሚው በመሰልጠን ላይ ናቸው አቶ ተወልደ እንደተናገሩት፡፡