ቻይና ከደቡብ ቻይና ባህር ጋር በተያያዘ የአውሮፓ ህብረትን አስጠነቀቀች
ህብረቱ የደቡብ ቻይና ባህርን በተመለከተ የሚሰጣቸውን ያልተገቡ አስተያየቶች እንዲያቆም አሳስባለች
ሁለት የፊሊፒንስ መርከቦች ያለፍቃድ ወደ ደቡብ ቻይና ባህር በመግባቸው በቻይና ተይዘዋል
ቻይና የአውሮፓ ህብረት የደቡብ ቻይና ባህርን በተመለከተ ከሚሰጣቸው አስተያየቶች እንዲቆጠብ አሳስባለች።
የአውሮፓ ህብረት የደቡብ ቻይና ባህርን አስመልክቶ የሚሰጣቸው ያልተገቡ አስተያየቶች በቀጠናው ሰላም እና መረጋጋት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሊፈጥር እንደሚችልም በአውሮፓ ህብረት የቻይና ቋሚ መልእክተኛ አሳስበዋል።
የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳዮች ተግባራት አግልግሎት “የፊሊፒንስ መርከቦችን በደቡብ ቻይና ባህር ላይ ታግተዋል” በሚል አስተያየት መስጠቱን ተከትሎ ነው በአውሮፓ ህብረት የቻይና ቋሚ መልእክተኛ ማስጠንቀቂያ አዘል ምልእክቱን ያስተላለፈችው።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርም ጉዳዩን በተመለተ ቀደም ብሎ አስተያየት ሰጥቶ የነበረ ሲሆን፤ በዚህም ሁለቱ የፊሊፒንስ መርከቦች ያለ ቻይና እውቅና ወደ ቻይና ናራይ ጂዮ በተባለ ስፍራ መግባታቸውን አስታውቋል።
የቻይና የባህር ጠባቂዎች መርከቦቹን በቁጥጥር ስር መዋላቸው በህግ አግባብ ስራቸውን ነው የሰሩት፤ ይህም የቻይናን የግዛት ሉላላዊነት ለማስጠበቅ የተሰራ ስራ ነው ብሎ ነበር።
መርከቦች በሚለቀቁበት አግባብ ላይ ቻይና እና ፊሊፒንስ ንግግር መጀመራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማሳወቁን ሲ.ጂ.ቲ.ኤን ዘግቧል።
ቻይና በደቡብ ቻይና ባህር ላይ ያላት ሉዓላዊነት፣ መብቶች እና ጥቅሞች የተባበሩት መንግስታት የባህር ህግ ስምምነትን ጨምሮ በአለም አቀፍ ህግ መሰረት ለረጅም ጊዜ ሲተገበረ መቆየቱንም አመላክቷል።
ቻይና የአውሮፓ ህብረት የደቡብ ቻይና ባህርን በተመለከተ የሚሰጠውን አስተያየት በፅኑ እንደምትቃወም የገለፀች ሲሆን፤ የአካባቢው ሀገራት ልዩነቶቻቸውን በአግባቡ ለመምራት እና በደቡብ ቻይና ባህር ላይ መረጋጋትን ለማስፈን የሚያደርጉትን ጥረት እንዲያከብርም ጠይቃለች።