ትግራይን ጨምሮ በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ተቀባይነት ያለውና ወደ ብሔራዊ እርቅ የሚወስድ የፖለቲካ ሂደት እንዲፈጠር የቡድን 7 ሀገራት ጥሪ አቀረቡ
የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ ግዛት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በፍጥነት እንዲወጡ የጂ 7 ሀገራት ጠይቀዋል
የቡድን 7 አባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በትግራይ ጉዳይ መግለጫ አውጥተዋል
የካናዳ ፣ ፈረንሳይ ፣ ጀርመን ፣ ጣልያን ፣ ጃፓን ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ዩኤስኤ የሚገኙበት የቡድን 7 ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እንዲሁም የአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ ተወካይ የትግራይን ወቅታዊ ጉዳይ በተመለከተ የጋራ መግለጫ አውጥተዋል፡፡
መግለጫው ሲጀምር “እኛ የካናዳ ፣ የፈረንሳይ ፣ የጀርመን ፣ የጣሊያን ፣ የጃፓን ፣ የዪናይትድ ኪንግደም እና የዩናይትድ ስቴትስ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እና የአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ ተወካይ ፣ በቅርቡ ሪፖርት የተደረጉ በትግራይ የተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እና በደሎች እንዲሁም የዓለም አቀፍ የሰብአዊ ሕግ ጥሰት በጣም አሳስቦናል” ይላል፡፡
መግለጫው አክሎም በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርስ ያለውን “ግድያ ፣ ጾታዊ ጥቃቶችን ፣ ያለ ልዩነት የሚፈጸም ከባድ ድብደባ እና በትግራይ ነዋሪዎች እና የኤርትራ ስደተኞች ላይ የሚፈጸመውን አስገዳጅ መፈናቀል” እንደሚያወግዙ ይገልጻል፡፡ ሁሉም ወገኖች የዜጎችን ደህንነት ማረጋገጥ እና የሰብዓዊ መብቶችን እና ዓለም አቀፍ ህጎችን ማክበር እንዳለባቸውም ነው የተጠቀሰው፡፡
በቅርቡ የኢትዮጵያ መንግስት ለእንዲህ ዓይነት ጥሰቶች ተጠያቂ መሆን ያለባቸውን ለመጠየቅ ላሳየው ቁርጠኝነት እውቅና የሰጠው መግለጫው መንግስት ቃሉን ተግባራዊ እንዲያደርግም ጠይቋል፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን (OHCHR) ፣ ከትግራይ ግጭት ጋር በተያያዘ የጋራ ምርመራ ለማካሄድ መስማማታቸውን በመጥቀስ ፣ በተዘረዘሩት የወንጀል ድርጊቶች ላይ ግልፅ እና ገለልተኛ የሆነ ምርመራ ማድረግ እና ለእነዚህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተጠያቂዎች በሕግ ፊት እንዲቀርቡ ማድረግ እንደሚያስገልግ መግለጫው አንስቷል፡፡
በግጭቱ ውስጥ ያሉ አካላት “ያልተገደበ ሰብዓዊ አቅርቦትን እንዲያቀርቡ እንጠይቃለን” ያሉት በየቡድን 7 ሀገራት “በማዕከላዊ እና በምስራቅ ትግራይ ሰፊ አካባቢዎች ሁኔታዎች እየተባባሱ መሆናቸው እና የከፋ የምግብ ዋስትና ችግር መኖሩ ያሳስበናል” ብለዋል፡፡
በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኤርትራ ኃይሎች ከትግራይ ይወጣሉ በሚል ያወጡትን መግለጫ በደስታ እንደሚቀበሉም መግለጫው ጠቁሟል፡፡ ይህ ሂደት በፍጥነት ፣ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መፈጸም እንዳለበትም ነው የተገለጸው፡፡
የቡድን 7 ሀገራት “አመጽ እንዲቆም እና ትግራይን ጨምሮ በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ተቀባይነት ያለው እና ወደ ተአማኒ ምርጫ እና ወደ ሰፊ ብሔራዊ እርቅ የሚወስድ ግልፅ ፣ ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ሂደት እንዲፈጠር ጥሪ እናቀርባለን” ብለዋል ፡፡
የሰብዓዊ ድጋፍ ጥረቶችን እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ የሚደረጉ ምርመራዎችን ለመደገፍ ዝግጁ እንደሆኑም የቡድን 7 ገገራት በመግለጫቸው አስታውቀዋል፡፡
በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በፓርላማ በሰጡት ማብራሪያ ፣ በርካታ ሀገራት በትግራይ ያለው የሰብዓዊ ችግር እንደሚያሳስባቸው ከመግለጽ ውጭ በተጨባጭ እዚህ ግባ የሚባል ድጋፍ እንደማያደርጉ መናገራቸው ይታወሳል፡፡ እስካሁን በክልለሉ ከቀረበው የሰብዓዊ ድጋፍ 70 በመቶ የሚሆነው በኢትዮጵያ መንግስት መሸፈኑንም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡ መንግስት ለሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት እንዲሁም ለሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ምርመራ ክልሉን ክፍት ቢያደርግም ፣ ምዕራባውያን ተግባራዊ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጫና ለመፍጠር ብዙ ርቀት እንደሚሄዱም ጠቁመዋል፡፡