በቻይና-አፍሪካ ጉባኤ ላይ ስኬታማ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ስምምነት የተፈራረሙ ሀገራት እነማን ናቸው?
ቻይና በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት ውስጥ 50 ቢሊዮን ዶላር ለአፍሪካ ድጋፍ አደርጋለሁ ብላለች
አፍሪካ እና ቻይና በታሪክ ምርጡን የወዳጅነት ጊዜ እያሳለፉ ነው ተብሏል
በቻይና-አፍሪካ ጉባኤ ላይ ስኬታማ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ስምምነት የተፈራረሙ ሀገራት እነማን ናቸው?
የቻይና አፍሪካ መሪዎች ጉባኤ በቤጂንግ እየተካሄደ ሲሆን የተመድ ዋና ጸሀፊን አንቶኒ ጉቴሬዝን ጨምሮ ከ50 በላይ የሀገራት መሪዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡
የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ፒንግ ባደረጉት የጉባኤው መክፈቻ ንግግር ቻይና እና አፍሪካ ከመቼውም ጊዜ በላይ ምርጥ ግንኙነታቸውን እያጣጣሙ ነው ብለዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ አክለውም ቻይና በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት ውስጥ 50 ቢሊዮን ዶላር ለአፍሪካ ትሰጣለች ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ከዚህ ውስጥም 25 ቢሊዮን ዶላሩ በብድር መልኩ ለአፍሪካ ሀገራት ይሰጣል የተባለ ሲሆን 11 ቢሊዮን ዶላሩ ደግሞ እርዳታ እንዲሁም 10 ቢሊዮን ዶላሩ ደግሞ የቻይና ኩባንያዎች ወደ አፍሪካ ሄደው ኢንቨስት እንዲያደርጉ የሚደረግ ድጋፍ እንደሚውል ተገልጿል፡፡
የገንዘብ ድጋፉ ለ1 ሚሊዮን አፍሪካዊያን የስራ እድል እንደሚፈጥርላቸው ፕሬዝዳንቱ በመክፈቻ ንግግራቸው ላይ ጠቅሰዋል፡፡
የዓለማችን ቁጥር ሁለት ባለግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆነችው ቻይና ከአፍሪካ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያላት ሲሆን ለዚህ ጉባኤ ወደ ቤጂንግ ያቀኑ ሀገራት አዳዲ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ስምነቶችን በማድረግ ላይ ናቸው፡፡
በነገው ዕለት ከሚጀምረው ከቻይና - አፍሪካ ትብብር ጉባኤ ምን ይጠበቃል?
ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር 17 የመግባቢያ ሰነዶችን መፈራረሟን ጠቅላይ ሚነስትር ዐቢይ አህደም (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስታውቀዋል።
ዛምቢያ ፣ ታንዛኒያ፣ ዚምባብዌ፣ ኬንያ እና ናይጀሪያ በርካታ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ስምምነቶችን ከቻይና ጋር ተፈራርመዋል፡፡
ታንዛኒያ እና ዘምቢያ የሚያስተሳስራቸውን የባቡር መሰረተ ልማት ግንባታ ከቻይና በሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ ለመገንባት ሲፈራረሙ፣ ዚምባብዌ አቭካዶ ምርቶቿን ወደ ቻይና ገበያዎች መላክ የሚያስችላትን የንግድ ስምምነት መፈራረማቸው ተገልጿል፡፡
ናይጀሪያ ደግሞ የወደብ ልማት፣ ነጻ የንግድ ቀጠና እና የትራንስፖርት መሰረተ ልማቶችን ለመገንባት ከቻይና ኩባንያዎች ጋር ተፈራርማለች፡፡
ዘምቢያ የታዳሽ ሀይል ኢንቨስትመንት ስትፈራረም ኬንያ ደግሞ የግብርና ምርቶቿን ወደ ቻይና አብዝታ መላክ የሚያስችላትን ከመፈራረሟ ባለፈ የባቡር መስመር ግንባታ ስምምነት እንደተፈራረመች ተገልጿል፡፡