ቻይና ከሩሲያ የምትሸምተውን ዩራኒየም መጠን በሶስት እጥፍ አሳደገች
ከሩሲያ ዩራኒየም በመግዛት ቀዳሚ የነበረችው አሜሪካ በአንጻሩ ግዥዋን በ30 በመቶ ቀንሳለች ተብሏል
ሞስኮ ከበለጸገ ዩራኒየም ሽያጭ በየአመቱ ከ2 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር በላይ ታገኛለች
ቻይና የሩሲያን ዩራኒየም በመግዛት ቀዳሚዋ ሀገር ሆነች።
ቤጂንግ ባለፉት አስር ወራት 849 ሚሊየን ዶላር የሚያወጣ የበለጸገ ዩራኒየም ከሞስኮ ያስገባች ሲሆን ይህም ከባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር በሶስት እጥፍ ጭማሪ ያሳየ መሆኑን የሩሲያው ብሄራዊ የዜና አገልግሎት አርአይኤ ኖሶስቲ ዘግቧል።
በጥቅምት ወር ብቻ 216 ሚሊየን ዶላር ዋጋ ያለው ዩራኒየም ከሩሲያ ወደ ቻይና መግባቱንም ነው ዘገባው የጠቀሰው።
ደቡብ ኮሪያ በ10 ወራት ውስጥ 650 ዶላር የሚያወጣ ዩራኒየም ከሩሲያ በመግዛት ሁለተኛዋ ሀገር ሆናለች።
በ2023 ቀዳሚዋ የሩሲያ ዩራኒየም ገዥ ሀገር የነበረችው አሜሪካ ደግሞ ግዣዋን በ30 በመቶ ቀንሳ (574 ሚሊየን ዶላር) ሶስተኛ ደረጃን መያዟ ተገልጿል።
ዋሽንግተን በዩክሬኑ ጦርነት ምክንያት በሞስኮ ላይ ጫና ለማሳደር ለኒዩክሌር ሃይል ማመንጫዎቿ የሚያስፈልጋት በዝቅተኛ ደረጃ የበለጸገ ዩራኒየም ከሩሲያ እንዳይገዛ መወሰኗ ይታወሳል።
የሀገሪቱ የኢነርጂ ሚኒስቴር ግን አማራጭ ከጠፋና የአሜሪካን ብሄራዊ ጥቅም ማስጠበቅ ያስፈልጋል ተብሎ ከታመነበት እስከ 2028 ድረስ የበለጸገ ዩራኒየም ከሩሲያ ተገዝቶ እንዲገባ ፈቅዷል።
ሩሲያ ከአለማችን ዩራኒየም የማብላላት አቅም 44 በመቶውን ትይዛለች።
የዋሽንግተንን የንግድ የኒዩክሌር ሃይል ማመንጫዎች ለማንቀሳቀስ ከሚያስፈልገው ዩራኒየም 35 በመቶው የሚገኘው ከሞስኮ ነው።
ይህም አሜሪካን ቁጥር አንድ የሩሲያ ዩራኒየም ተጠቃሚ ሀገር ቢያደርጋትም የዩክሬኑ ጦርነት የሞስኮና ዋሽንግተንን የንግድ ግንኙነት እየጎዳው ይገኛል።
ሩሲያም ባለፈው ሳምንት በደምብ የተብላላ ዩራኒየም ወደ አሜሪካ እንዳይገባ በጊዜያዊነት ማገዷን ተከትሎ የዩራኒየም ዋጋ መጨመሩን ሬውተርስ ዘግቧል።
ሩሲያ በአለማቀፍ ደረጃ ከሚካሄደው የበለጸገ ዩራኒየም ሽያጭ 40 በመቶ ድርሻ አላት። የአለማችን ግዙፉ የዩራኒየም ማብለያ ያላት ሞስኮ ከምርቱ በየአመቱ ከ2 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር በላይ ታገኛለች።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሀገራቸው በምዕራባውያን ለተጣሉባት ከ16 ሺህ በላይ ማዕቀቦች ምላሽ ለመስጠት እንደ ዩራኒየም ያሉ ስትራቴጂካዊ ፋይዳ ያላቸው ምርቶች ሽያጭ ሊገድቡ እንደሚችሉ በመስከረም ወር መናገራቸውን አርቲ አስታውሷል።