ኢራን የኒዩክሌር መሳሪያ ለመስራት በተቃረበ ደረጃ ዩራኒየም እያበለጸገች ነው ተባለ
የበለጸገ ዩራኒየም ክምችቷ ሶስት አቶሚክ ቦምቦችን መስራት እንደሚያስችልም ነው ለአለማቀፉ አቶሚክ ሃይል ኤጀንሲ የቀረበ ሪፖርት የሚያሳየው
ቴህራን በበኩሏ ዩራኒየምን ለሰላላማዊ የሃይል ምንጭነት እንጂ ለኒዩክሌር ጦር መሳሪያ መስሪያነት አላውልም ባይ ነች
ኢራን የኒዩክሌር መሳሪያ ለመስራት በተቃረበ ደረጃ ዩራኒየም እያበለጸገች መሆኑ ተጠቆመ።
ቴህራን 35 የቦርድ አባላት ካሉት የአለማቀፉ አቶሚክ ሃይል ኤጀንሲ ጋር ባለፈው አመት መጋቢት ወር የደረሰችውን ስምምነት ተፈጻሚ እያደረገች አለመሆኑንም ሁለት አባል ሀገራት ያቀረቡት አዲስ ሪፖርት ያመላክታል ብሏል ሬውተርስ በዘገባው።
ሪፖርቱ ኢራን ያከማቸችው 60 በመቶ ንጹህ ዩራኒየም እስከ ግንቦት 11 2024 ድረስ 142.1 ኪሎግራም መድረሱንም ነው የጠቆመው።
ይህን የተከማቸ ዩራኒየም ወደ 90 በመቶ ደረጃ ከፍ አድርጋ ካበለጸገችው ሶስት አቶሚክ ቦምቦችን መስራት እንደሚያስችል ባለሙያዎች ያብራራሉ።
የበለፀገ ዩራኒየም የማብላያ ነዳጅ ብቻ ሳይሆን የኒዩክሌር ቦምቦችን ለማምረትም ሊያገለግል ይችላል። ይሁን እንጂ በጦር መሳሪያዎች ደረጃ የሚያገለግለው ዩራኒየም 90 በመቶ ድረስ መበልጸግ ይኖርበታል።
የኢራኑ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ በሄሊኮፕተር አደጋ ህይወታቸው ማለፉ የመንግስታቱ ድርጅት የኒዩክሌር ተቆጣጣሪ ተቋም እና ኢራን የጀመሩትን ንግግር እንዳስተጓጎለው ተገልጿል።
ፈረንሳይ እና ብሪታንያም በቀጣዩ ሳምንት በሚደረገው የአለማቀፉ የአቶሚክ ሃይል ኤጀንሲ የቦርድ ስብሰባ በቴህራን ላይ አዲስ ውሳኔ እንዲተላለፍ መጠየቃቸው ነው የተሰማው።
ባለፈው ወር በቴህራን ጉብኝት ያደረጉትና ከሀገሪቱ ባለስልጣናት ጋር የመከሩት የኤጀንሲው ሃላፊ ራፋኤል ግሮሲ ተቋማቸው በኢራን የኒዩክሌር መርሃ ግብር ላይ የሚያደርገውን ቁጥጥር በተመለከተ የሚካሄዱ ንግግሮች በሚፈለገው ፍጥነት መቀጠል አለመቻላቸውን አንስተዋል።
ግሮሲ በወቅቱ “ኢራን ፍላጎቱ ካላት በርካታ ኒዩክሌር ቦምቦችን ለመስራት የሚበቃት የበለጸገ ዩራኒየም አከማችታለች” ማለታቸውም የሚታወስ ነው።
ከጋዛው ጦርነት በኋላ ከእስራኤል ጋር ሚሳኤል የተወራወረችው ኢራን ኒዩክሌርን ከሰላማዊ አላማ ውጪ አልጠቀምበትም በሚለው አቋሟ እንደጸናች ነው።
አንዳንድ ባለስልጣናቷ ግን የቴል አቪቭና ምዕራባውያን ጫና እና ጸብ አጫሪነት በዚሁ ከቀጠለ የኒዩክሌር ፖሊሲያችን መለወጡ አይቀርም የሚሉ አስተያየቶችን እየሰጡ ነው።