የአሜሪካ ሴኔት የሩሲያ ዩራኒየም ወደ ሀገሪቱ እንዳይገባ ወሰነ
ዋሽንግተን ለኒዩክሌር የኤሌክትሪክ የሃይል ማመንጫዎቿ ከምትጠቀመው ዩራኒየም 12 በመቶውን ከሩሲያ ነው የምታስገባው
አሜሪካ በሩሲያ እና ቻይና ኩባንያዎች ላይ አዲስ ማዕቀብ መጣሏ ተሰምቷል
አሜሪካ ለሩሲያ የጦር መሳሪያ ግብአቶችን ያቀርባሉ ባለቻቸው የቻይና ኩባንያዎች ላይ ማዕቀብ ጣለች።
በአዲሱ ማዕቀብ በመቶዎች የሚቆጠሩ ከሩሲያ የጦር መሳሪያ ልማት ጋር ግንኙነት ያላቸው ኩባንያዎችና ግለሰቦች መካተታቸውን የሀገሪቱ ግምጃ ቤት አስታውቋል።
ከተቃዋሚው አሌክሲ ናቫልኒ ግድያ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ግለሰቦችም የግምጃ ቤት ሃላፊው ጃኔት የለን ተናግረዋል።
16 የቻይና እና ሆንግ ኮንግ ኩባንያዎችም ለሩሲያ የጦር መሳሪያ ግብአቶችን አቅርበዋል በሚል ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል ነው ያሉት።
የአሜሪካ የግምጃ ቤት ሃላፊው ባለፈው ወር ወደ ቤጂንግ በማቅናት ቻይና ለሩሲያ የጦር መሳሪያም ሆነ ግብአቶች ድጋፍ እንዳታደርግ ማሳሰባቸውን አሶሼትድ ፕረስ አስታውሷል።
ከሞስኮ ጋር ኢኮኖሚያዊ ትስስሯ ይበልጥ እየጨመረ መሄዱን የምትገልጸው ቤጂንግ የዋሽንግተንን ወቀሳ ውድቅ ስታደርግ ቆይታለች።
የአዘርባጃን፣ ቤልጂየም፣ ስሎቫኪያ እና ቱርክ ኩባንያዎችም ለሩሲያ የጦር መሳሪያ ግብአቶች በመላክና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ በአሜሪካ ወቀሳ ቀርቦባቸዋል።
በሌላ ዜና የአሜሪካ ህግ መወሰኛ ምክርቤት (ሴኔት) ከሩሲያ ዩራኒየም ማስገባትን ለማቆም የቀረበ የውሳኔ ሃሳብን ማጽደቁ ተሰምቷል።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በህጉ ላይ ፊርማቸውን እንደሚያኖሩ ይጠበቃል።
አሜሪካ ለኒዩክሌር የኤሌክትሪክ የሃይል ማመንጫዎቿ ከምትጠቀመው ዩራኒየም 12 በመቶውን ከሩሲያ ነው የምታስገባው።
የአሜሪካ የዩራኒየም እገዳ ሩሲያን 1 ቢሊየን ዶላር ያሳጣታል ተብሏል።
ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት እንደጀመረች ከሞስኮ ነዳጅ ማስገባቷን ያቆመችው ዋሽንግተን ከሩሲያ ዩራኒየም ጥገኝነት እንድትወጣ ተደጋጋሚ ጥሪ ሲቀርብላት ቆይቷል።