ቻይና የዓለም ጤና ድርጅት የኮሮና መነሻን ለማጥናት ያቀረበውን ጥያቄ ውድቅ አደረገች
የቻይናው ምክትል የጤና ሚኒስትር ግን የድርጅቱን ጥያቄ ቻይና አትቀበልም ብለዋል
ቻይና ለምርመራው ተባባሪ እና ግልፅ እንድትሆን የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ ጠይቀዋል
የዓለም ጤና ድርጅት የኮሮና ቫይረስን መነሻ ምክንያት በቻይና ውስጥ ለማጥናት ያቀረበውን ጥያቄ ቤጅንግ ውድቅ ማድረጓን አስታወቀች፡፡
ድርጅቱ የኮሮና ቫይረስ መነሻ ምክንያትን ለመመርመር ለ2ኛ ዙር ስራ ቻይናን ቢጠይቅም ሀገሪቱ ግን ፈቃደኛ አለመሆኗን የቻይና ምክትል የጤና ሚኒስትር አስታውቀዋል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት በቻይና ቫይረሱ መጀመሪያ በተገኘበት አካባቢ ያሉ ቤተ ሙከራዎችን ኦዲት ለማድረግ ቢፈልግም ምክትል የጤና ሚኒስትሩ ዜንግ ይዥን ግን ይህ ሳይንስን አለማክበርና መናቅ ነው ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡
የድርጅቱ ባለሙዎች ቫይረሱ ከቤተ ሙከራ አምልጦ ነው የሚለው ወደ እውነት የመቅረብ ዕድል እንደሌለው ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጅ አሁንም የኮሮና ቫይረስ ከውሃን ከተማ ቤተ ሙከራ አምልጦ መሰራጨቱን የሚገልጹ አሉ፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ባለሙያዎች ውሃን ከተማ ለመሄድ ዕቅድ ተይዞላቸው እንደነበር የሚታወስ ቢሆንም የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም (ዶ/ር) አሁንም ቀጣይ ምርመራ በቻይና እንዲደረግ ማዘዛቸው ተገልጿል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ ቻይና ለምርመራው ተባባሪ እና ግልፅ እንድትሆን ጠይቀዋል፡፡
የቻይናው ምክትል የጤና ሚኒስትር ግን የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርን ሃሳብ ተቀባይነት እንደሌለው አንስተዋል፡፡